Wednesday, May 20, 2020

የትንሣኤ አሰላስሎዬ ከሆስፒታል አልጋዬ ላይ (ራቪ ዘካርያስ)


ራቪ ዘካርያስ፦
የትንሣኤ አሰላስሎዬ ከሆስፒታል አልጋዬ ላይ[1]

  
ይህን የምጽፈው በቴክሳስ ከሚገኘው የካንሰር ሕክምና መስጫ ሆስፒታል ውስጥ ኾኜ ነው። ከኹለት ወራት በፊት በጀርባዬ ላይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ባደረግሁ ጊዜ  ሳርኮማ (sarcoma)  የሚባል፥ ዐልፎ ዐልፎ የሚከሠትና አኹን እየታከምሁት ያለ የካንሰር ሕመም ዐይነት እንደተገኘብኝ ሲነገረኝ ደንግጨ ነበር። ለብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር የተባረከና ጤናማ ሕይወት ነበረኝና፥ ይህን ዜና መስማት ማስደንገጡ አይቀረም።

ኹልጊዜም፥ በትንሣኤ መልእክት ኀይል አምናለሁ፤ አኹን ደግሞ፥ የበለጠ አምናለሁ። ከማናቸውም ተስፋዎች ኹሉ የበለጠ ታላቁ መልእክት እርሱ ነው፤ በርግጥም፥ ታላቁ የተስፋ መደላድልም እርሱው ነው።

በአልጋዬ ላይ ጋደም እንዳልሁ ፍጥረታዊው ዓለም መንፈሳዊ እውነታዎችን ለማስረዳት እንዴት ሊያንጸባርቃቸው እንደሚችል ሳሰላስል ነበር። ካንሰር ማለት ራሱን በእርባና ቢስነት እያራባና እውነተኛ ሕይወት ሰጪ ሕዋሳትን እየተሽቀዳደመ የሰውን ሕይወት በየቀኑ በአንድ እርምጃ ወደ ሞት የሚያስጠጋ ወስላታና ብልሹ ሕዋስ ነው። አፈንጋጭ ሕዋስ። ይህ ነገር የነፍሳችን ጠላት አዳምና ሔዋንን፥በውኑ እግዚአብሔር ተናግሯልን?” በማለት [በእግዚአብሔር ላይ] ጥያቄ እንዲያነሡ ባደረጋቸው ጊዜ፥ በዘፍጥረት መጽሐፍ የምናነበውንና የውድቀትን ታሪክ ለማገናዘብ የሚያግዝ አስገራሚ ነጸብራቃዊ ተምሳሌት ኾኖ አግኝቸዋለሁ። [ቅድመ አያቶቻችን] ሕይወት ሰጪ የኾነውን እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ከመምረጥ ይልቅ ያለመታዘዝና የራስን ፈቃድ በራስ የመወሰን ወስላታ ሕዋስ አፈንግጦ እንዲገባባቸውና በሰው ዘር ኹሉ ውስጥ ያለምንም ገደብ እንዲሠራጭ (metastasize እንዲያደርግ) ፈቅደውለታል።

እንደሚታወቀው፥ እኛ የሰው ልጆች፥ ይኸንን ካንሰር የተባለ ወስላታ ሕዋስ ለመዋጋት፥ በጋራ ኾነን ቢሊየን ዶላሮችን እየከሰከስን በምንፍጨረጨርበት በዚህ ወቅት፥ በዋናነት ኹለት የህክምና አማራጮች ብቻ ከፊታችን ቀርበውልናል፤ እነርሱም፥ አስቸጋሪዎቹን አፈንጋጭ ሕዋሳት ለመረፍረፍ የሚሰጠው የጨረራ (radiation) ሕክምና እንዲሁም፥ አሰልቺ ድግግሞሽ የማያጣውና የተቀናጀ ዘዴን የሚጠቀመው ኬሞቴራፒ  (chemotherapy) ናቸው። ይኹንና፥ እነዚህ የካንሰር ሕክምና መንገዶች በጨለማ ውስጥ የሞውዜር ቃታን ስቦ እንደ መተኮስ ዐይነት ናቸው፤ ምክንያቱም [በሕክምና መንገዶቹ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች] አፈንጋጮቹን ሕዋሳት ብቻ ሳይኾን መልካሞቹን ሕዋሶቻችንን ጭምር ይጨረግዷቸዋልና። በመኾኑም፥ የማታ ማታ ድሉ ቢገኝ እንኳ፥ ምናልባት ከድል ተነሺው ይልቅ ድል መቺውን ዋጋ ስለሚያስከፍለው፥  ድሉ እያነቡ እስክስታዐይነት ድል (pyrrhic) ሊኾን ይችላል።  

ፍጹሙ አምላካችንና መድኀኒታችን


በእግዚአብሔር ላይ ባመፅን ጊዜ፥ የመድኅን፥ ሊያውም የፍጹም መድኅን፥ አስፈላጊነት በእግዚአብሔር ኢኮኖሚ ውስጥ የቀረልን ተስፋ ኾነ። ያን ፍጹም መድኅንም፥ ራሱ እግዚአብሔር በገዛ ልጁ አዘጋጀልን። ይኸም ነገር፥ እግዚአብሔር የእያንዳንዱን ግለ ሰብ ሕይወት እንዴት ዋጋ እንደ ሰጠው የሚያመለክት እውነት ነው። ነቢያቱ አስቀድመው እንደ ተናገሩት፥ አዳኙ ይመጣል። በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በመሞት ይቀበራል። በአስደናቂው የትንቢት ቃል መሠርትም፥ ኢየሱስ በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ፤ ድል ነሺው በእውነት ድል ነሣ። ሕይወት ሰጪው መንፈስም ተመልሶ ተሰጠን።  

እንግዲህ እኛም ከሐዋርያው ጋር ይኸን ጥያቄ ማንሣት እንችላለን? “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?(1 ቆሮ. 1555) ኀጢአት በውስጣችን ብልሹው የካንሰር ሕዋስ ነው። ነገር ግን፥ የኢየሱስ ሕይወት፥ ሞትና ትንሣኤው ለእግዚአብሔርን የፍጥረት ሥርዐት በሚጠቅም መንገድ ሞገዱን ቀለበሰው። ስለዚህ፥ ይኸን በዓለ ትንሣኤ በልባዊ ደስታ እናክብረው፤ በሞት መካከልም ሕይወትን አንፈልግ፤ ምክንያቱም መቃብር ድል ነሺ አይደለም። አያሸንፍም። [ትንሣኤው] የውድቀት ኀይል ላይመለስ የተቀለበሰበትና ታላቁ ፈውስ በማያዳግም ኹኔታ የተሰጠበት ድል ነው።  

የዬሉ ኒኮላስ ዎልተስቶፍ፥ ልጁን በከፍታ የመውጣት አደጋ በሞት በተነጠቀ ጊዜ፥ እንዳለው፥ሰውን በቅርብ ማጣትን ጣጣ ስልክ በመደወል፥ ክንፍ አልባነትን በአውሮጵላኖች፥ የበጋ አየር ጸባይ የሚያስከትለውን የሙቀት ቃጠሎን በአየር ጸባይ መቈጣጠሪያ ማሽኖች ለመቋቋም አላዳገተንም፤ እነዚህንና ሌሎች ያልተጠቀሱ ጕድለቶችን ለማስወገድና ችግሮቻችንን በሚገባ ለመቋቋም ችለናል። ነገር ግን፥ ልንመክታቸው የሚገባ ኹለት መሠረታዊ ችግሮች ተደቅነውብን ቀርተዋል፤ እነርሱም በልባችን የሚያድረው እኵይ እና ሞት ናቸው። 

እንግዲያውስ፥ መልሱ ያለው እዚህ ጋ ነው። መልሱ ያለው፥ ሞት የሚወልደውን የዐመፅ ሕዋስን ለማደባየትና ሕያው ሕዋሳትን በእኛ ውስጥ ለማደስ በሚችለው የእግዚአብሔር ልጅ ብርሃን ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ምንኛ ውብ እውነት ነው! ምን ዐይነት የተስፋ መልእክት ነው!

ስለ መስቀሉ እያሰላሰልንና ከሞት የተነሣውን ጌታችንን እያከበርን ባለንበት ጊዜ በመደነቅና በአምልኮተ እግዚአብሔር እንሞላ። [በዚህ ወቅት] ከተሞቻችን በሞት ሽታ እየታጠኑ ነው። የሕይወት መዓዛ ሽታ ያስፈልገናልስሙም ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል። 



[1] ይህ ጽሑፍ በሚያዚያ 2 ቀን 2012 .. Gospel Coalition ገጽ ላይ የታተመ ሲኾን፥ በዚህ መልክ ወደ አማራኛ መልሼዋለሁ። https://www.thegospelcoalition.org/article/easter-reflection-hospital-bed-zacharias/