Monday, October 24, 2011

ስሙን መልሱልን


ስሙን መልሱልን[1]

በሰሎሞን አበበ ገ/መድኅን


ከበርካታ ወራት በፊት በተንቀሳቃሽ ስልኬ በተላከልኝ አጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) ላይ አንድፍተላብጤ አነበብኩ፡፡ፍተላውየሚያስፈግግ ነገር ነበረው፡፡ ኾኖም ግን ድንጋጤው በቅጡ ነዝሮኛል፡፡ ነገርዬው እንደሚለው፣ አንድ የሃይማኖት አባትአንድ ወርኀዊ በዓል በነባሮቹ ላይ አከሉ፡፡ ይኸውም፤ 1 ልደታ፣3 በኣታ፣5 አቦዬ፣ 6 ኢየሱስ፣ 7 ሥላሴ፣ 8 ቢዮንሴይላል፡፡ ይህ ሥላቅ ያላስፈገገኝ በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ ሁለተኛው፣ የሕዝብህን አለቃ አታንጓጥጥ (ዘዳ. 22÷28 የሐዋ. 23÷5) የሚለውን ቅዱስ መርሕ ስለጣሰ ነው፡፡ አንደኛውንና ዋነኛውን ምክንያት ደግሞ በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ላይ አመላክታለሁ፡፡

ብዙ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሐውልት እንዲሠራላቸው ተናዘዙ ሲባል  ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ወይም በስማቸው የመታሰቢያ ድርጅት ሲያቋቁሙ ተመልክታችኋል፡፡ አሊያም በሕይወት እያሉ፣ የንግድ ወይም የይዞታ ተቋሞቻቸው ላይ ስማቸውን ሲያኖሩ አይታችኋል፡፡ ለምን ብትሉ ግን ምላሹ ስማቸውን ስለሚወድዱ ነው የሚል ይኾናል፡፡ ማንም ሰው ስሙን አቆላምጠው ሲጠሩት ደስ ይሰኛል፡፡ ለማብሸቂያ በተሰጠውቅጥልስም በተጠራ ጊዜ የሚፈነድቅ ሰው ገጥሟችሁ ያውቃል? አይመስለኝም፡፡ ወይም ደግሞ ስሙን/ስሟን ሳትጠቀሙ እንዲያው በደፈናውአንተአንቺእንትናማነህማነሽብላችሁ በመጥራትስ ያስደሰታችሁት ሰው ነበርን? ይህም አይመስለኝም፡፡ ስም የየሰዉ መታወቂያው ነውና (ሁሉም ባይባል እንኳን) ብዙኀኑ ለስሙ ይቈረቈራል መሰል፡፡ ዛሬ ዛሬ ለምናየው የየቤተ ዕምነታችን ትርምስ አንዱ ምክንያት ስምና ዝናን የማጕላት አባዜ ስለተጠናወተን ነው የሚሉ ወገኖችም ገጥመውኛል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ይመስለኛል።

ስም፣ ክብርና ዝና በዓለማችን ለተከሰቱ ታላላቅ ጦርነቶች መነሾ ኾነዋል፤ እየኾኑም አለ፡፡ አዎ! ስም ያጋድላል፣ ያባላል ያጣላል፡፡ ስሜ አልተጠራም፣ ሥራዬ አልተወሳም፣ ተዘለልኩ፣ ከሌሎች አንሼ ታለፍሁ፣  በሚሰኙና በተመሳሳይ ሰበብ ይኸው ስንት አሰቃቂ ተግባር ሲፈጸም ይኖራል፤ ተፈጽሟልም፡፡ ወደ ዝርዝሩ መግባት ውቅያኖስን በማንኪያ ለመጨለፍ እንደመሞከር ነውና ለጊዜው እንለፈው፡፡


የዚህ ኹሉ ወግ ዋነኛው ትኵረት እንግዲኽ ወደ አንድ ዐቢይ ጕዳይ ለመንደርደር ነው፡፡ይኸውም፣ ስም ያለን እኛ ብቻ አለመኾናችንን በማሰብ እንደ ስሙ የኾነና መኾንም የሚችል ባለ ስምና ባለዝና እያለ፣ ነገር ግን ባለማስተዋል ስሙ የተደበቀበት ባስ ሲልም  ስሙንየተነጠቀስለ መሰለኝ አካል ለማውሳት ነው፡፡ እርሱምእኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” (ኢሳ. 42÷8) ያለው እግዚአብሔር ነው፡፡ በርግጥ ይህ ኃይለ ቃል የተነገረው የሕያው እግዚአብሔርን ስም በአሕዛብ ጣዖታት በመለወጥ፣ ከመንገድ የወጡትን እስራኤላውያን ለመንቀፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬም የአምላካችን ስም በአግባቡ ሳይከበር የሚቀርብባቸው ሌሎች ኹኔታዎች መኖራቸው አልቀረም፡፡

ይህ ምጥን ጽሑፍ ስለ እግዚአብሔር ስም ዝርዝር በመስጠት ለማስተማር የሚጥር ትንታኔ አይደለም፡፡ አንባቢዎቼም ለዚህ እውነት ባእድ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ እውነተኛው አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር (ዮሐ. 17÷3) እጅግ የገነነ፣ እንደ ባሕርይውና ማንነቱ የኾነ ስም ያለው ነው፡፡ ስሙ ራሱን እሱነቱን የሚወክል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም የአስተርዕዮው (የመገለጡ) ነጸብራቅ ነው (ዘጸ. 3÷1415 ሆሴ. 12÷6)፡፡ ስሙን የምንጠራውም በተገቢው ኹኔታና ስፍራ በክብር ሲኾን (መዝ.96÷2 100÷4 105÷1) ስሙ ራሱን ይወክላልና (1ነገ. 8÷17-2029) ያድነናል (የሐዋ. 4÷10-12)፡፡
 
ኾኖም ይህ እውነት እንደ ዘበት የተጣሰባቸው ጥቂት ያልተገቡ ጕዳዮችን በማንሣት እርምት የሚሹ ግድፈቶችን ላወሳ እወዳለሁ፡፡ ቀጥሎ በቀረቡት አምስት አስረጂዎች አማካይነትም ምሳሌ አመላክትና፣ በአጽንኦትስሙን መልሱልን!” እላለሁ፡፡

አሐዱ፡-አንተማን?


የመጀመሪያውና የአምላካችን ስም እንዲመለስልን የምንጠይቅበት ቦታ በዝማሬዎቻችን ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ በርካታ አጠያያቂ እክቶች የታጀሉበት እንደኾነ የሚታማው የዝማሬ አገልግሎት፣ ጠንካራ ሒሳዊ ግምገማዎች ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩበት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ጽሑፍ የዝማሬን አላባዎች በማንሣት ሙያዊ ክህሎትን የተንተራሰ አስተያየት ለመስጠት አይቃጣም፡፡ ከቶ በምን አቅሙ! ኾኖም ከርእሰ ጕዳያችን ጋር በተያያዘ አንዳንድ መዝሙሮችን (መዝሙር ከተባሉ) ልብ ብለን ካዳመጥናቸው፣ ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድረስ አንድም ጊዜ (ልብ በሉ! አንድም ጊዜ ነው ያልኩት) እንኳን የእግዚአብሔርን ስም አይጠሩም፤ ወይም አያነሡም፡፡ (መቼምበመጽሐፈ አስቴርም ውስጥ አልተጠቀሰም እኮ!› እንደማትሉኝ እተማመናለሁ) በምትኩአንተወይምእርሱበሚሉ ተውላጠ ስሞች ብቻ የተቀነበቡ ኾነው ተገኝተዋል፡፡ ለዋቢነት የተወሰኑትን መጠቃቀስ ተገቢ ቢኾንም እነርሱን የማሰስን ኃላፊነት ለአንባቢው መተዉ ተመርጧል፡፡ ስመ ድንቁ አምላክ እግዚአብሔር ራሱን የገለጠባቸውና የሚጠራባቸው እርሱን፣ ማንነቱን፣ ሥራውንና ባሕርይውን የሚወክሉ ስሞች እያሉትአንተብቻ ተብሎ መታለፉ እጅግ አጠያያቂ ሲብስም አሳፋሪ ይመስለኛል፡፡

ለመኾኑ፣ በዐውዱ ውስጥ አንድ ጊዜ እንኳ መለኮታዊ ስሙ ካልተጠቀሰ በስተቀር ተውላጠ ስም  ብቻውን የዘላለሙን አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን ስለ ማመልከቱ ምን ማስረጃ ይኖረናል? አገልጋዮቹስእግዚአብሔርን አንዲያገለግሉና በእግዚአብሔር ስም እንዲባርኩ…” (ዘዳ.21÷5) አይገባምን? እርሱም ኪዳኑን የሚጠብቅና ርስቱን የማያስነውር ነውና “…ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም” (1ሳሙ. 12÷24)፡፡ ደግሞም፣እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ።” (ኢሳ. 12÷4 በተጨ. መዝ. 105÷1) ተብሎ ተጽፏል፡፡ 

እንደው ለመኾኑ፣ ስለ ኃጢአታችን ራሱን አሳልፎ የሰጠውንና ከሞት የተነሣውን የታላቁን የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ከዝማሬዎቻችን ደብቀን ማንን ልናውጅ ይኾን? ሰሚ ያገኘ እንደኾን መጽሐፍስ እንዲህ ያዛል፣በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ” (ኤፌ.2÷1920)

ክልዔቱ፡- “እስስስ


በቀጣይነት የማነሣው በርኵሳን መናፍስት ቊጥጥር ሥር ለወደቁ ሰዎች በሚደረግ ጸሎት ጊዜ ከአንዳንድ ወገኖች አንደበት የሚደመጠውን አባባል ነው፡፡ ርኵሳን መናፍስት ከተቈጣጠሩት ሰው ውስጥ የሚባረሩት ድል በነሣቸው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው (ማር. 16÷17 ሉቃ. 10÷17)፡፡ ከዚህ ውጭ በማንኛውም ስም፣ በየትኛውም መንገድና ዘዴ አጋንንት ሊወጡ አይችሉም፡፡ ወጣሁ ቢሉም አልወጡም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ሰይጣንን ሲገስጹ ሳለ የጌታን ስም በግልጽ ከመጥራት ይልቅ! !”ቱም! ቱም!...” ወይም........ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ፣እስስ... ውደቅ!” ይላሉ፡፡ ምን ማለት ይኾን? መጽሐፉ ያስተማረን፣ ጋኔልን፣እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ (የሐዋ. 16÷18) ብሎ ማባረርን አይደለምን?

ሠለስቱ፡-  እንዴት ልጻፈው? እግዚአብሔር፣እግ//እግ.” ወይስእግዚ”?


አስቀድሞ በብዙዎች እጅ ጽሑፍና በግል ማስታወሻዎቻቸው ላይ የተለመደና አሁን አሁን ግን ለኅትመት በበቁ መንፈሳዊ መጽሔቶችና በየግድግዳና ምሰሶዎች ላይ በምንለጣጥፋቸው የማስታወቂያ ፖስተሮች ላይ ሳይቀር የምመለከተው የእግዚአብሔርን ስም  ለመጻፍ የምንሞክርበት መንገድ ሌላኛው አስገራሚ ኹነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን ከገለጠባቸው ስሞቹ መካከል ያህዌ ኤሎሂም አልፎ አልፎም ኤል ኤላህ እና አዶን የተሰኙትን መለኰታዊ ስሞች በመወከል በግዕዝ፣ በአማርኛና ትግርኛ ቋንቋ አገልግሎት ላይ የዋለው ስም እግዚአብሔር የሚለው ነው፡፡ ይህ ስም በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ በሕግም ይኹን በክርስቲያናዊ ነገረ መለኰት ሥርዐት በምህጻረ-ቃል የሚጻፍበት መንገድ የለም፡፡ ይኹንና፣ በርካታ ክርስቲያኖች በዘፈቀደ  “እግ/ወይም/እግ.” ወይምእግዚበማለት ለሕዝብ ዕይታና ንባብ በተዘጋጁ ጽሑፎች ላይ እንደዘበት ጽፈውልን አይተናል፤ እያየንም ነው፡፡ ይህ አጻጻፍ ጸያፍና በፍጹም ጥቅም ላይ ሊውል የማይገባው ነው፡፡ አንባቢዎቼን ካላስቸገርኳችሁ አስቲ ስሞቻችሁን በሁለትና ሦስት ፊደላት እያሳጠራችሁ ተመልከቱት፡፡ ይህን ለማድረግ ብንሞክር የአንዳንዶቻችን ስም ምናልባት አስነዋሪ ትርጕም ያለው ነገር ይወጣው ይኾናል፡፡
 
ጕዳዩን በሌላ ምሳሌ ለማየት እንሞክር፤ መንግሥታዊው ልሳን አዲስ ዘመን በርእሰ- አንቀጹ ስለ ክቡር /ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተግባር አቋሙን እየተነተነ ስማቸውን ሲያነሣ ሳለ፣መለ. ዜዊ.” በማለት ቢጽፍስ ብላችሁ አስቡ፡፡ ውጤቱ ሕፁፅ ብቻ ሳይሆን ጸያፍና አስነዋሪ ይኾናል፡፡ ታዲያ የንጉሠ ነገሥታትና የጌታዎች ጌታ የልዑል እግዚአብሔር ስም አጻጻፍስእባካችሁ ስሙን መልሱልን!

ኣርባዕቱ፡- የማን ናት አላችሁ?


ይኽኛው አስረጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተለመደ የመጣ ሲኾን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልኾነ የባለቤትነት መግለጫን ይመለከታል፡፡ አንዳንድከተሜነትየሚሰማቸው ክርስቲያኖች አባል ስለኾኑበት፣ ወይም ስለሚያገለግሉበት፣ አሊያም በዕለቱ መንፈሳዊ አገልግሎት ስለተካፈሉበት ጕባኤ የት መኾን ሲጠየቁ ወይም ስለዚያች ማኅበረ ምዕመናን የሚሉት ነገር ኖሯቸው ሲያነሡየፓስተር እንቶኔ ቤተ ክርስቲያንሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ ዛሬ በምድራችን ላይ በመጋቢዎቻቸው ስም ብቻ የሚታወቁና የሚጠሩ አያሌ ቤተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ኾኖም የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደሚያስተምረው ቤተ ክርስቲያን በገዛ ደሙ የዋጃት የእግዚአብሔር ናት (ሐዋ.20÷28)፡፡ በድፍረትምቤተ ክርስቲያኔማለት የሚችል ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው (ማቴ.16÷16)፡፡ ይህ ቀላል መስሎ የታያችሁ ካላችሁ አባባላችሁ ስሁት ነውና ስሙን መልሱ!

ሓምስቱ፡-ከበደል የማይርቀው” 


ዐሠርቱ ትእዛዛት መካከል ሦስተኛው ዘወትር ከሚጣሱት ሕግጋት አንዱ ነው፡፡በኢየሱስ ስምየተሰኘው ሐረግ የየጨዋታው፣ የፌዙና ስላቁ ማዳመቂያ ስለመኾኑ ዋቢ ጥራ መባል አይኖርብኝም፡፡አሁን አሁን ደግሞ የሆሊዉዱን! ማይ ጋድእንዲተካ ዘንድ መሰለኝ የእኛው ሕዝብ አጫዋች (ኮሜዲያን) ያስተዋወቀውን! ማይ ክርስቶስየተሰኘ ብሂል የትንፋሻቸው ያህል የሚያለከልኩበትም ገጥመውኛል፡፡  

ግን ልብ በሉ! ስሙ የጌታችንና የመሲሐችን ስም ነው (ማቴ.1÷21)፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች የኾንነው በእርሱ ስም በማመናችን ነው (ዮሐ. 1÷12)፡፡ መሲሕ ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን ራሱን አዋርዶ ለመስቀል ሞት የታዘዘ ኾነ፡፡ አብም ከስም ኹሉ በላይ የኾነውን ስም ሰጠው (ፊል. 2÷10-11)፡፡ በእርሱም ስም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ኹሉ ይሰበክ ዘንድ የተገባ ኾነ (ሉቃ. 24÷47)፡፡ ታዲያ ይህን ስም ምን ያህል ልናከብረው በተገባ! ለዚህም ይመስለኛል በቅዳሴ እግዚዕ ላይ እንዲህ የምናነብበው፣ስመ ዚአከ ይስማእ ሞት ወይደንግፅ፤ ወቀላያት ይሰጠቃ፤ ወጸላዒ ይትከየድ፡፡ መንፈሰ ኀጕል ይርዐድ፤ ወከይሲ ይትገኀሥ፣ ወኢአሚን ይርሐቅ፤ መዓት ይኅሣዕ፤ ቅንዓት ኢይብቋዕ፤ ዝሉፍ ለይትገሠጽ፡፡ያንተን ስም ሰምቶ ሞት ይደንግጥ፣ ቀላያትም ይሠንጠቁ፣ ጠላትም ይረገጥ፡፡ የጥፋት መንፈስም ይንቀጥቀጥ፤ ከይሲም ይወገድ፤ አለማመንም ይራቅ፤ቊጣ ጸጥ ይበል፤ ቅናት ጥቅም አያግኝ፣ ኃጢአትን የሚያዘወትር ይገሠጽ።

እንግዲህ በመግቢያዬ ላይ በተጠቀሰው ስላቅ ለምን እንዳልተደሰትሁ መናገር ወደሚገባኝ ቦታ ደረስኩ መሰለኝ፡፡ መልእክቱን ወደ እኔ የሰደደው ሰው ክርስቲያን ነበር፡፡ ለዚያ ሰውና መልእክቱን ይለዋወጡ ለነበሩት ሌሎች በርካታ ወገኖች ነገሩ ተራ ቀልድ ብጤ ኖሯል፡፡ እናም በዚያው ዘና መሰኘታቸው በራሱ ክፋት የለበትም ይኾናል፡፡ በእግረ- መንገዱ ሊስተዋል የሚገባው ዐቢይ እውነት ግን አለ፡፡ በስላቁ ዝብዝብ ውስጥ የጌታ ስም እንደ ዘበት "ጣል" ተደርጓል፡፡ በርግጥ አሳፋሪ ይመስለኛል፡፡ በታላቁ ትእዛዝ ውስጥ እንደታወጀው፣ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያርቀውም ይልም አይደል (ዘጸ. 2÷7)?፡፡  እናም፣ በተመሳሳይ መንገድ ስሙን የምትጠቀሙ ክቡር ስሙን ወደ ክቡር ሥፍራው መልሱ፡፡
 
መጽሐፉም አስፈሪ ስሙን ለሚንቁ አስፈሪ ብድራት እንደሚጠብቃቸው ይናገራልአስደናቂና አስፈሪ የኾነውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ስም ባታከብርእግዚአብሔር አስፈሪ መቅሰፍትበአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል” (ዘዳ. 28÷58) ሲል፡፡
 
ስሙን በማክበር ተስማምተን እንደኾነእግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ” (መዝ. 34÷3)። እናም፣ እስቲ ይህን አብረን እንበል! “አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ”(ማቴ.6÷ 9)! 
ሎቱ ክብር ወስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤ ወአሜን!



[1] ይህች መጣጥፍ ከዚህ በፊት በማቴቴስ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 14 ላይ የወጣች ነበረች፡፡

4 comments:

  1. What can we say then? We hear those titles here and there. Sometimes it seems they are singing for their soul mate. May God gives us wisdom to see the critic in the right way and suppose to be. Love you!!

    ReplyDelete
  2. "ሥምን መልአክ ያወጣዋል" እንዲሉ የዚህ የመጦመሪያ ገጽ ስያሜ ና የተነሳው ርእሰ ጉዳይ እጅግ በጣም የተጣጣጣሙ ናቸው። ከሁሉ በላይ ግን የሚገርመኝ እና ቀልቤን የሳበው ጉዳይ ለነገሮችህ ማስረጃ ምትጠቀማቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው። እንዴ ምን ማለቱ ነው የሚል ጥያቄ ለማንሳት ልዘጋጅ ሳስብ ቀጥሎ ያለውን ጥቅስ ሳነብ ውስጤ የሚፈጠር ጥያቄ ሁሉ ይጠፋል። ሌላው ደግሞ የአገላለጽ ዘይቤህ በጣም ደስ ይላል:'አንጀት አርስ' የሆኑ አገላለጾች ናቸው:: የጦመርክበት ጉዳይ ደግሞ ሁላችንም የምናውቀው ነገር ግን በማን አለብኝነት የተውነው ብሎም ከተዘረዘሩት ግድፈቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱን ፈጻሚዎች ነን፤ ስለዚህም በግሌ ትልቅ ማስታወሻ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እግዚአብሄር ይባርክህ።
    በእውነትም ድንቅ ስም ነው ያለው ኢየሱስ! "የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።" መጽሐፈ ምሳሌ 18፥10

    ReplyDelete
  3. Stunning language and compelling message. I loved every single line of it. God bless you!

    ReplyDelete
  4. መልዕክትህን ብቻ ሳይሆን እንደ እሳት የሚነድ ቅንዓትህን ጭምር ነው ያነበብኩት፡፡ጽናቱን ይስጥህ! ሌላ ምን ይባላል፡፡

    ReplyDelete