Friday, April 18, 2014

መስቀሉን ሰቀሉት

መስቀሉን ሰቀሉት




በዚያ ጊዜ የተከናወኑ ድንቅ ነገሮች ስፍር ቍጥር ላቸውም። አምላክ በመስቀል ላይ ዋለ፤ ፀሓይ ጨለመች፣ ብርሃኗንም ከለከለች፤ ፍጥረት ለፈጣሪው ዐዝኗልና። የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተሠነጠቀ፤ ደምና ውሃም ከጌታ ጐን ፈሰሰ፤ አንደኛው ሰው እንደመኾኑ፣ ሁለተኛው ከሰው በላይ በኾነው ማንነቱ። ምድር ተናወጠች፣ ዐለቶችም ተሠነጣጠቁ፤ ይመጣ ዘንድ ያለውን መላለማዊ ትንሣኤንም ይመሰክሩ ዘንድ ከቅዱሳን ሥጋዎች መካከል የተወሰኑቱ ከሙታን ተነሡ።... በውኑ በመቃብሩ ዘንድ የተከናወኑትን በሙሉ ሊተርክ የሚችል ማን ነው? ነገር ግን የትኛውም ድርጊት ከመዳኔ ተኣምር ጋር ሊወዳደር አይችልም። ጥቂት የደም ጠብታ መላውን ዓለም ዐደሰው። በወተት ውስጥ ኾኖ ወተትን እንደሚያጣብቀው ፈሳሽ ደሙ የሰውን ዘር አንድ ላይ አያያዘው።


—ጐርጐርዮስ ዘኢንዚናንዙ

እንደ መንደርደሪያ


ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የዓለም መድኀኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ (ማር. 1524 ዮሐ. 1918) ደሙን በማፍሰሱ ምክንያት፣በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኝተናል፤ እርሱም የበደላችን ስርየት” (ኤፌ. 17) ነው።ደም ሳይፈስ ስርየት የለም (ዕብ. 922) ስለዚህ ክርስቶስ ደሙን ሰጠ። ዐዲሱ ኪዳን ተመርቆ በተከፈተበትና (ዕብ. 91518) የኀጢአታችን ማስተሰረያ ይኾን ዘንድ በመስቀል ላይ በፈሰሰው ንጹሕ ደሙ (ቆላ. 119) አማካይነት ታጥበን (ራእ. 15) በመንጻት ወደ እግዚአብሔር መግባት ኾኖልናል (ሮሜ. 52 ኤፌ. 218 ዕብ. 1019-20)። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

እንግዲህ ይህን እውን ለማድረግ መድኅኑ ጌታ ኢየሱስ ስለ ኀጢአታችን የሞተው በእንጨት ላይ ነበር።ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ጴጥ. 224) ተብሎ እንደ ተጻፈ። ይህ የመስቀል ላይ ሞቱ የመከራና የህማም ጣር የተሞላ ነበር። አዳኙ ጌታ በፈቃዱ ለአባቱ በመታዘዝ እንደ ሎሌ ነበር የኖረውና ያገለገለው (ፊል. 26-9 ኢሳ. 421-7 491-6 504-9 53 1-13) ሊያውም የህማም ጣርና ሥቃይ ያልተለየውሥቅዩው ሎሌ (The Suffering Servant) ነበር። በመጨረሻም፣ሥቅዩው ሎሌድኅነትን ያስገኝልን ዘንድ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ። የተሰቀለው መሲሕ ተባለ (ማቴ. 261-2756)

ከዚህም የተነሣ፣ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ሁለት ዓመታት መስቀሉን ማእከል ያደረገውን ወንጌል ስታበሥር ኖራለች፤እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ቆሮ. 123) እያለች። የመንግሥቱ ወንጌል ቤዝዎታዊ እውነቱ የሚታየው ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኩል ነውና። ያልተዋጁ ንጉሡንም ኾነ መንግሥቱን አያዩትምና። ስለዚህ በዚህ ዐጭር ጽሑፍ ውስጥ የመስቀሉን ምንነት ለማመልከት ጥረት ተደርጓል።

በአንጻሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጭ በኾነ ትምህርትና ኑሮ የመስቀሉን መልእክት አዛብታ የተገኘችበት ወቅትም ነበረ፤ ዛሬም አለ። ከእነዚህ ግድፈቶች መካከል የተወሰኑትን ማለትም ከሥቅዩው ሎሌ ይልቅ ማሠቃያውን፣ የመከራው ተካፋይነት ከሚገለጥበት የመስቀል ኑሮ ይልቅ ምልክታዊ ጌጥነቱን ማስቀደማችንን እንዲሁም መስቀሉን ማእከል ካደረገው ትምህርት ይልቅ ቅምጥልነትን የሚያስፋፋውንዘመነኛውን ወንጌልማስቀደማችንን በማንሣት እንታረምበት ዘንድ ዐጭር ሐሳብ አስፍሬአለሁ። ይህን ሐሳብ በቅንነትና በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ስር ኾነን እንድናነብም እማጠናለሁ።

ለመኾኑ መስቀል ምንድነው? ፋይዳውስ ምንድነው? እንግዲያስ ስለ ነገረ መስቀሉ ትንሽ ማየት ያስፈልግ ይመስለኛልምልክትነቱና ክብሩ የሚገባን ያን ጊዜ ነውና! ምልክቱ ከወከለው እውነት በላይ አይደለምና! ደግሞም የመስቀሉ በረከቶች ከመስቀሉ የመከራ ሕይወት ተነጥለው አይገኙምና! ለመኾኑ መስቀል ለክርስትና እምነት ምኑ ነው?

ነገረ-መስቀሉ


ይህ ሰፊና ጥልቅ ርእሰ ጕዳይ በጥቂት ገጾች የሚተረክ እንዳልኾነ ግልጽ ነው። ነገር ግን በተፈቀደልኝ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለመቅረብ በሚችል መልኩ እንዲሁም ለውይይታችን መነሻ እንዲኾን በማሰብ ከዚህ እንደሚከተለው ጠቅለል ባለ መልክ ለማቅረብ እሞክራለሁ። በየሐሳቦቹ ሥር ያኖርኋቸውን የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ክፍሎችን በሙሉ እዚሁ ማንበብ ባይቻለን እንኳ፣ ጽሑፉ በሚደርሰን ጊዜ በግላችን ክፍሎቹን በማየት ሐሳቦቹን ማገናዘብ እንችላለን። ይህን ካልን እንግዲህ ነገረ መስቀሉን፣ በጨረፍታ፣ እንደሚከተለው እናየዋለን።

ሰው በአምሳለ ሥላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው። እግዚአብሔር በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮታልና (ዘፍ. 126-28) እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በአጽናፈ ዓለሙ ካሉት ፍጥረታት በሙሉ የተለየና ክቡር አድርጎ ነው። ሁሉን በቃሉ ብቻ ሲፈጥር ሰውንከምድር አፈር አበጀው” (ዘፍ. 27)በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስንእፍአለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (ዘፍ.27)

እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፥ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.127)  ያዘጋጀለት መኖሪያውም ያማረና የተሟላ የአትክልት ስፍራ ነበረ።እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው” (ዘፍ. 28) በምድርና በባህር የሚኖሩትን በሰማይም የሚበሩትን እንዲገዛ እግዚአብሔር ለሰው ሥልጣን ሰጠው (ዘፍ. 1÷26-28) ታላቁ አምላክ በማይነገር ጥበቡና ፍቅሩ ሰው በብርሃን የተሞላ የክብርና የጽድቅ ሕይወት ይጎናጸፍ ዘንድ ባለሟሉ አደረገው። ሊቁ ጎርጎርዮስ እንዳለው፣ ምንትኑ ይከብር እም ዝንቱ ማዓረግ ወአይ ምክሕ የዐቢ እምኵሉ ትምክሕትወይኩን ስምዐ ከመ ውእቱ ገብሮ ለእጓለ እመሕያው በአርአያሁ ወበአምሳሊሁ።ከዚህ ክብር የሚበልጥ ምን ክብር አለ? ከዚህስ ትምክሕት የሚበልጥ ምን የሚያስመካ ነገር አለ?...ሰውን በርሱ አምላክ እንደ ፈጠረው እንዲመሰክር ከመሆን የበለጠ ምን ትምክሕት አለ?”[1]

ለሰው የተሰጠው ታላቁ በረከት  ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት መኖሩ ነበር። የሕይወት ምንጭ ከኾነው አምላክ ጋር በሚኖር ኅብረት ብቻ ሕይወት በክብርና በብርሃን ትቀጥላለችና (መዝ. 369 ዮሐ. 14) ይህን ለማረጋገጥም በመታዘዝ መኖር ይጠበቅበት ነበር። የመታዘዙ ምልክትምክፉና ደጉን ከሚያስታውቀው ዛፍአለመብላት ነበር። ከዚህ ዛፍ በበላ ቀን እንደሚሞት (ከእግዚአብሔር መለየትን የሚያካትተው መንፈሳዊ ሞትን ጨምሮ) እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው (ዘፍ. 215-17)

ሰው የመረጠው የዐመፃ መንገድ ግን አስፈሪ ነበር። ከአምላኩ ይልቅእባቡየነገረውን በማመን እግዚአብሔርንሐሰተኛ ለማድረግ ተጣደፈ። በራሱ ያለ እግዚአብሔር መኖር እንደሚቻለውና እንዲያውምእንደ እግዚአብሔር ለመኾን ተመኘ (ዘፍ. 35) አዳምና ሚስቱ ሔዋንም የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ በመብላት በእግዚአብሔር ላይ የተገዳዳሪነት ዐመፅ ፈጸሙ (ዘፍ. 31-6 1ጢሞ. 214) በዚህም ምክንያት ኀጢአት ወደ ዓለም ገባ (ሮሜ 512) ውጤቱም ሞት፣ ኀዘን፣ ውርደትና ውድቀት ኾነ (ዘፍ. 3) በመተላለፋችንና በኀጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለየን (ኤፌ. 21-3)

አዳምና ሔዋን የሰው ዘር ሁሉ ወላጆች እንደ መኾናቸው፣ በሠሩት ኀጢአት ምክንያት ለመላው ልጆቻቸው ያወረሱት በኀጢአት የወደቀ ባሕርይን ነው (ሮሜ 512-14 ኤፌ. 23) አባቶችጥንተ አብሶ” (የውርስ ኀጢአ) ብለው የሰየሙት የኀጢአት ተፈጥሮ ሁሉንም የተጠናወተው በመኾኑ፤ በኀልዮ፣ በነቢብ፣ በገቢር (በሐሳብ፣ በቃል፣ በሥራ) ኀጢአተኛ አደርጎን ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በአካል ክፍሎቻችን ሁሉ ይሠራ ነበር (ሮሜ 75) የኀጢአት ውጤቱ ደግሞ ሞት (ከእግዚአብሔር መለየት) በመኾኑ ከኵነኔ በታች ወድቀን ተከረቸምን (ሮሜ 623) እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ አምላክ በመኾኑ፣ ኀጢአታችን ከእርሱ ለይቶን ነበርና (ኢሳ. 592)

ነገር ግን ጨለማው እንደነበር እንዲቀጥል መለኮት ዘላለማዊ ምክር አልፈቀደም። እግዚአብሔር በመቤዠት ጥበቡ የፈረሰውን ሊሠራው፣ የወደቀውን ሊያነሣው፣ የተበላሸውን ሊያድሰው ፍቅሩና ጥበቡ ቤዛችንን ገለጠው። የዚህ ሰማያዊ ድነት (ድኅነት) አጀንዳ መካከለኛው ደግሞ መስቀሉ (የክርስቶስ ቤዛዊ ሞት) ነበር። ከአብ ጋር በክብር የተካከለ ወልድ ወረደ፤ እስከ መስቀል ሞትም ድረስ ራሱን አዋረደ (ፊልጵ. 25)ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ፤ ወአብጽሖ እስከ ለሞትፍቅር፣ ኀያል ወልድን ከዙፋኑ ሳበው፤ እስከ ሞትም አደረሰውእንዲል።

ጌታ ኢየሱስ ኀጢአታችንን ተሸክሞ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ (ማቴ. 2735 1ጴጥ. 224) የኀጢአታችንን ቅጣት ተቀበለ (ኢሳ. 535-6) ታላቁ እግዚአብሔር በመስቀል ላይ በሞተው በልጁ ሞት ምክንያት የእያንዳንዳችንን መከራ፣ ሞትና እርግማን አስወግዷል (ኢሳ. 534 ገላ. 313) በዚህም አደራረጉ ጻድቅ ፈራጅነቱን አሳይቷል (ሮሜ. 325-26) እንዲሁም፣ አንድ ልጁን በመስጠት እግዚአብሔር ፍቅሩን በመስቀሉ ላይ ገለጠልን (ሮሜ. 54) ላመንን ለኛም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ዐዲስ በር ተከፈተልን (ዕብ. 1019-20) በመስቀሉ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ዐዲስ ኅብረት ለመመሥረት በቃን። በመስቀል ላይ በፈሰሰው በኢየሱስ ደም የኀጢአታችንን ስርየት ስለምንቀዳጅ (ቆላ. 112-14 1ዮሐ. 21-2) በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተናል (2ቆሮ. 521) ስለኾነም፣ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ” (መዝ. 8510) የሚለው እውነት በመስቀሉ ላይ ተፈጸመ።

እግዚአብሔር በጻድቅ ፈራጅነቱ በኀጢአታችን ላይ ከበየነው ፍርድ፣ በሩቅ ብእሲ ቤዛነት መዳን ስለማይቻለን፣ አንድያ ልጁን ነው የሰጠው (ዮሐ. 316) ጌታ ኢየሱስም በፈቃዱ ስለ ኀጢአተኞች ሞተ (ዕብ. 109) ይህ ተግባር ደግሞ የፍቅሩን ጥልቀት የሚያሳይ ነው (ሮሜ. 54) ትክክለኛ ፍርዱንና ፍቅሩን በአንድነት እውን ያደረገው ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። ከመታወቅ የሚያልፈው ይህ ድንቅ ጥበቡ ደግሞ በክርስቶስ የመስቀል ሞት ተገለጠክርስቶስ የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ነውና (1ቆሮ. 123-24)! ስለዚህምየመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።” (1ቆሮ.118) ተባለ። ሎቱ ስብሐት ለዓለመ ዓለም፤ አሜን!

የመስቀሉ ፋይዳዎች


መስቀሉ ከዓለም መጀመሪያ በእግዚአብሔር የዘላለም ዕቅድ ውስጥ የነበረ ነው። የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እውን ኾነ። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞቱ ያስገኛቸውን በረከቶች በሙሉ መዘርዘር ባይቻልም፣ ጥቂት ነጥቦች ብቻ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

1.     ልንጠየቅበት ለሚገባን ኀጢአት ሁሉ እግዚአብሔር መፍትሔ ሰጥቷል።

ታላቁ ጌታ በመስቀል ላይ በዋለው ልጁ ሞት አማካይነት የሁላችንን ኀጢአት፣ መከራ፣ ሞትና ኀዘን አስወግዷል። ኢየሱስ የሞተው ኀጢአተችን ሊያስከፍለን የሚችለውን ሞትና ጥፋት ለማስወገድ ነው። በመስቀሉ ላይ ያደረገልንን ምክንያት በማድረግ በንስሐ ስንመለስ የኀጢአታችን ስርየትና ይቅርታ እንቀበላለን።

እግዚአብሔር ኀይሉን በመስቀሉ ላይ ገለጠ (1 ቆሮ. 118 ሮሜ. 116) ፍቅሩንም በመስቀሉ ላይ አሳየን (ሮሜ. 58) ኀዘናችንን በመስቀሉ አስወግዶታል (ኢሳ. 534) ስለዚህም፣ ቅጣታችንን በቤዛነቱ ኢየሱስ ወስዶልናልና የምናምን ሁሉ ከኀጢአት ቅጣት ድነናል (ኢሳ. 535-6 1ጴጥ. 2)። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

2.     በመስቀሉ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም ርስ በርሳችን ዐዲስ ኅብረት መሥርተናል።

እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ በመኾኑ፣ ኀጢአት ከእግዚአብሔር ይለየናል። ማንም በልቡ እንኳ የኀጢአት ሐሳብ እያለ በእግዚአብሔር ፊት ሊቆም አይችልም። በመኾኑም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ መሞቱ ብቻ ሳይኾን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ (ሮሜ 51-3) በግላችን እግዚአብሔርን እንድናውቀውና ከእርሱም ጋር ኅብረታችን ታድሶ ፍቅሩን ደስታውንና ሰላሙን እንድንካፈል ሊያስችለን ነው የሞተልን። ቢሊ ግርሃም በአንድ ወቅት እንዳሉት፣እግዚአብሔር ሰውን መውደዱን በመስቀል ላይ አረጋግጧል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙ ሲፈስና ሲሞት እግዚአብሔር ለመላው ዓለምእወዳችኋለሁብሎ ማወጁ ነበር።በዚህ ፍቅር ምክንያት ኅብረት ሥርተናል። ስለዚህም፦

·        በመስቀሉ በኩል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አገኘን (2 ቆሮ. 521)
·        በመስቀሉ በኩል ይቅርታን (የኀጢአት ስርየትን) እንቀበላለን (ቆላ. 112-14 1 ዮሐ. 21-2)
·        በመስቀሉ በኩል የተባረከውና ቅዱስ የኾነው የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አባል ኾነን እንካተታለን (ዕብ. 21-12 ዮሐ. 112)
·        በመስቀሉ በኩል የወገን (የዘረኝነት) ግድግዳ ፈራርሷል (ኤፌ. 212-16)


3.     መስቀሉ አርነት አውጥቶናል።

በመስቀሉ ሥራ አማካይነት ከታሠርንባቸው ባርነት ሰንሰለቶች ሁሉ ነጻ ወጥተናል። የተወሰኑት እኒህ ናቸው፦
o   ከሰይጣን ኀይል ነጻ ወጥተናል (ቆላ. 113 215)
o   ቀድሞ ከሠራነው ኀጢአትና ከዕዳው ሁሉ ነጻ ወጥተናል (ዮሐ. 836 ቆላ. 213)
o   ከሚታገለን የኀጢአት ኀይል ነጻ ወጥተናል (ሮሜ. 614)
o   ከማንኛውም ዐይነት መርገም ኀይል ነጻ ወጥተናል (ገላ. 313 ከዘዳ. 2815-68 ጋር አነጻጽሩ)
o   ከኵነኔ ነጻ ወጥተናል (ሮሜ. 81 ዕብ. 926-27)
o   ከዘላለም ሞት ነጻ ወጥተናል (ዮሐ. 316)

4.     ፍቅርና ጽድቅ (ምሕረትና ፍርድ)በመስቀሉ ላይ ይገናኙ ዘንድ የመለኮት ጥበብና ኀይል ተገለጠ

መስቀሉ የእግዚአብሔር ፍቅርና የእግዚአብሔር ፍትሕ የተገናኙበት ቦታ ነው። ጽድቅ የተሞላው ፍርዱ የኀጢአት ዋጋ (ደመወዝ) የኾነውን የሞት ቅጣት ይጠይቃል። ፍቅሩ ደግሞ የራሱ የኾነውን ስለጠየቀ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞተ። በመስቀሉ ላይም የእግዚአብሔር ፍቅርና ትክክለኛ የፍትሕ ዳኝነቱ ተገናኙ (ሮሜ 321-26 58-11 1 ቆሮ. 123-24)

 እንግዲያስ መስቀልን እንዴት እንገንዘበው?

አጽንዖት ለመስጠት እንዲያግዘን አሁን ወደ ተነሣንበት ጥያቄ እንመለሳለን፤መስቀል ምንድነው?”ወደሚለው። የቃሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አጠቃቀም ስናይ፣ መስቀል በሦስት መንገድ ይተረጐማል። አንደኛው ሰው ለቅጣት ይሰቀልበት የነበረ ቀጥ ያለ ወይም የተመሳቀለ እንጨት ነው። ክርስቶስም የሞተው በእንጨት መስቀል ላይ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የክርስቶስን ወጆአዊ (ቤዝዎት) ሥራ ትዕምርታዊ ትክ (symbolic representation of redemption) የሚያመለክት ነው። ሦስተኛው ትርጓሜው ደግሞ ስቅለትን ራሱን (በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞትን) ያሳያል።[2] አማኞች ስለ ክርስቶስ የሚቀበሉት መከራ፣ ስደትና ሞትም በዚሁ ውስጥ ሊጠቃለል ይችላል።

እንግዲህ ቀደም ባሉት ገጾች ባጭሩ እንዳየን፣ መስቀል የታሪከ- ድኅነት መካከለኛ የኾነው የቤዛችን የክርስቶስን መከራና ሞት፣ ደሙን ማፍሰሱና በአጠቃላይም የቤዛነቱን ሥራ የሚያመለክት እንደኾነ በሚገባ አጢነናል (ኤፌ. 216 ቆላ.214) መድኀኔ ዓለም ሊቤዠን ራሱን ለሞት የሰጠው በመስቀል ላይ ነበርና። እኛ የምንሰብከውም የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው (1ቆሮ.123) በመስቀል ላይ የሚሞት የተረገመ አልነበረምን (ዘዳ. 2123)? ነገር ግን፣ ስለ እኛ ርግማን ኾኖ ከሕግ ርግማን ይዋጀን ዘንድ መሲሕ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቀለ (ገላ.313)! ርግማናችን የተወገደበት ከመኾኑ የተነሣ ግን ምልክታዊ ቦታ አለው። የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም ይህንኑ ሲያመለክቱ፣በኦሪትም ሥርዓት በመስቀል፤ በስቅላት የሚቀጡ ሁሉ ርጉማን ዉጉዛን ነበሩ። ከጌታ በኋላ ግን የነጻነታችን ዐዋጅ የተነገረበት ሰላማዊ ዙፋን ስለኾነ ለክርስቲያኖች ሁሉ የነጻነት፣ የድል ምልክት ነው።ገብረ ሰላመ በመስቀሉክርስቶስ ሰላምን እኩልነትን በመስቀሉ አድርጓልና[3] ይላሉ።

እንግዲህ ይህንን ታላቅና ክቡር የክርስትና እውነት ለማስታወስና ለማሳየት በቤተ ክርስቲያን ትውፊት የተመሳቀለ እንጨት (የዕፀ መስቀል) ምልክት ከክርስትና ጋር ተዛንቆ ይገኛል። ይህ በራሱ የሚያሳፍር አይደለም። አሳዛኝ የሚኾነው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ካዳነን ጌታ ይልቅ ክርስቶስ ተሰቅሎ የሞተበት የተመሳቀለ እንጨት ምልክት ካልተሰገደለት ብለን በማሰብ ይህንኑ ማድረግ ሲቃጣን ነው። ሕይወት ያለው በምልክቱ ላይ ሳይኾን ምልክቱ የሚጠቍመው እውነት ላይ ነውና። እውነቱ ደግሞ የጌታችን ቤዛዊ ሞት በመስቀል ላይ መፈጸሙ ብቻ ነው።

የመስቀል ምልክት ከላይ በተመለከትነው ምልክታዊ ፋይዳው በክርስትናው ዓለም ሁሉ ትውፊታዊ ቦታ አለው። ቄስ ኮሊን ማንሰል ስለዚህ ሐሳብ ሲጽፉ፣መስቀል የክርስትና ምልክት ነው። መስቀል በየቤተ ክረስቲያኑ ላይ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ በካህናት ልብስ ላይወዘተ ይታያል። ቄሶች በእጃቸውም ኾነ በኪሳቸው መስቀል ይዘው ይሄዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም መስቀልን በአንገታቸው ያንጠለጥሉታል። መስቀል ክርስቶስ የተሰቀለበትና የስቅለት ታሪክ መታሰቢያ ነው[4] ብለዋል።

የምንሰግድለት ግን በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ለሞተልንና ሞትን አሸንፎ ለተነሣው ንጉሣችን ነው (ራእ.5) ሃይማኖተ አበው፣እንከሰ ተሰቅለ እግዚእነ ወንሕነኒ ንሰግድ ለዘተሰቅለ ወወረደ ውስተ መቃብር ወተንሥአ እምኔሃ አመ ሣልስት ዕለት ወዐርገ ሰማያትእንኪያስ የተሰቀለው የክብር ባለቤት ነው። እኛም ለተሰቀለው ወደ መቃብር ለወረደው በሦስተኛው ቀን ለተነሣው ወደ ሰማይም ለዓረገው እንሰግዳለን[5] በማለት የሊቁን ሐሳብ አስፍሯል። ሃሌ ሉያ!

መስቀልን አስመልክቶ በትምህርተ ኅቡአት ላይ የተጻፈውን ስንመለከት ደግሞ እጅግ ያስደምመናል። ወበእላ ከናፍር ጾታ ነጊር ኢይትከሀል ጥንቁቀ፤ ዘእምትካት ኅቡአ ኮነ ይእዜሰ ክሡተ ምስጢረ ኮነ ለምእመናን፤ አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይትሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወቦቱ ንትመካህ ከመ ንሰብሖ በእነዚህ ከንፈሮች ጠንቅቆ የመናገር ስልት ሁሉ የማይቻል ነው። ከጥንት ስውር የነበረው ዛሬ ግን ለምእመናን የተገለጠ ሆኗል። እናመሰግነው ዘንድ የምንመካበት ይህ መስቀል በልብ የሚታሰብ ረቂቅ ነው እንጂ በዐይን የሚታይ ግዙፍ ነገር አይደለም።[6] እንዴት የሚደንቅ ነው!

ኧረ፣ የኛ ነገር! “መስቀሉን ሰቀሉት” እንዳይኾንብን


ይህ ቃል ተጋፋጭ መኾኑን እገነዘባለሁ። የእግዚአብሔር ሕዝብ መስመር በጣሱ ጊዜ የተነቀፉበትን መንገድ በማቆላመጥ እንዳልተቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የቤተ ክርስቲያን አንደኛው ተልእኮዋ ነቢያዊ ተጋፋጭነት ነው። ይህንን ሐሳብም የመረጥሁት በዚህ መንፈስ ነው። መስቀሉን ሰቀሉት! እንዴት አድርገው ሰቀሉት? ወይም እንዴት አድርገን ነው የሰቀልነው? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርምና፣ እነግራችኋለሁ።
ለምሳሌ በታሪክ ተመዝግቦ የቀረውን የመስቀል ጦርነት (ክሩሴድ)[7]ይሉትን አሳዛኝ ተግባር አስታውሱ። በአውሮጳ የነበሩ ክርስቲያን ነን የሚሉ ወገኖች ጦር ሰብቀው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ዘመቱት መስቀል አንግበው ብቻ ሳይኾን ጦርነቱን በመስቀል ስም ሠይመው ነበር። ስለ መስቀል መልእክት እንዲሞቱ የተጠሩ ክርስቲያኖች በመስቀል ስም ሊገድሉ ሲሄዱመስቀሉን ሰቀሉትሊባል አይገባምን? ይህ እንግዲህ የዓለማቀፉ ክርስትና ታሪካችን ውስጥ የነበረ ጠባሳችን ነው።

ወደ ቤታችን ደግሞ እንምጣ። መስቀል በቤዝዎት ታሪክ ውስጥ ከነበረው ቦታ የተነሣ የክርስትና አርማና ምልክት ተደርጎ መወሰዱ ይታወቃል። ይህ በራሱ ችግር የለውም። ነገር ግን የመስቀሉ ምልክት በራሱ የተለየ መድኀኒትነት እንዳለው ማሰብና ማስተማር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊነት የለውም። በታሪካችን ውስጥ እንዲያውም ይህን አለማድረግ የሚያስቀጣበትና የሚያስነቅፈበት ጊዜ ነበረ፤ አለም። ለምሳሌ ያህልፀረ ማርያምከሚለው ቀጥሎየመስቀል ጠላትየሚለው ነቀፌታ በኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ባሕልና ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ የራሱን አሉታዊ ሻራ ካሳረፉ አባባሎች ውስጥ ይመደባል። በነዚህ ስያሜዎች አማካኝነት የማይወዱትን ሰው/ቡድን ስምና ዝና ማጨቅየት በጣም ቀላል ኾኖ ኖሯል።

አስቀድመን የነገሩን የትመጣነት በአጭሩ እንመልከተው። ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ አድር ባይ ጋሻ ጃግሬዎቹን ጨምሮ፣ በአገዛዝ ዘመኑ የተነሡትን የወንጌል አገልጋይ መነኮሳት፣ ማለትም አነ አባ እስጢፋኖስ (ዐምደ ሃይማኖት ወማኅቶት ቤተ ክርስቲያን ዘጕንዳጕንዲ) አባ  አበ ከረዙል፣ አባ ዕዝራንና ሌሎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን ለመፍጀት የተጠቀሙበት ዋነኛ ክስፀረ- ማርያምና ፀረ- መስቀል ናቸውየሚል ነበር። ንጉሡ በዐዋጅ ባስነገረው መሠረትም ለማርያም ስዕልና ለመስቀል ቅርፅ መስገድ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን ዜግነታዊ ግዴታ ኾኖ ተቈጠረ (ማንም ሰውይህን ማድረግ እምነቴ አይፈቅድምብሎ ሳይሰግድ በዜግነቱ መኖር አይችልም ነበርና) ለመስቀል ምልክት መስገድ ብሔራዊ ግዴታ ኾኖ ነበር ማለት ነው። መስቀሉን ሰቀሉት ይሉሃል እንግዲህ ይህ ነው። ጌታ የሞተበት መስቀል ምልክት ሌሎችን መግደያ ሰበብ ኾነ ማለት አይደለም?

ምን ይህ ብቻ! ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ፤ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ፤ለእነዚህ ሁለቱ ፍጥረታት [ለማርያምና ለመስቀል] የፈጣሪ ክብር ይገባቸዋል፤ በክብር [ከእርሱ ጋር] ተካክለዋልና።[8] ሲል የስሕተት ዐዋጁን ያለኀፍረት ሊያስጽፍ በቅቷል። ይህ ማለት የመስቀል ምልክት ወደ ፈጣሪነት ክብር እንዲመጥቅ ተሰቀለ ማለት አይደለም? ይህ ታዲያ አይሰቀጥጥም?

ንጉሡ ለማርያምና ለመስቀል ቅርፅ መስገድን ጨምሮ ሌሎች እንግዳ ትምህርቶችን የማይቀበሉትን ክርስቲያኖች በዘግናኝና አሠቃቂ መንገድ ያሳድድ፣ ያገልልና ይገድል እንደነበር ወዳጆቹ ነን የሚሉ ሳይቀር በኩራት ጽፈዋል።[9] አፍንጫቸውን እየፎነነ (እየጐመደ) እጅ እግራቸውን እየከላ መነኰሳቱን ከነቆባቸው ተከታዮቻቸውንም ከነሳዱላቸው በደም ነክሮ ጨፍጭፏቸዋል። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተረጐሙት ገድለ አበው ወኣኀው ላይ እንዲህ ተጽፏል፤በትምህርቱ [በአባ እስጢፋኖስ ትምህርት] የዳኑና ከሕይወት በር የደረሱ ብዙ ናቸው።በድብ ፀር (በዘርአ ያዕቆብ) ዘመን ዘብር ከምትባል ሀገር ጀምሮ ደብረ ብርሃን ዝማ፣ ጐዘም እስኪደርስ፣ ከነዚህ አገሮች በስተግራ በኩልና በንጉሡ አደባባይም ሁሉ ሰማዕትነታቸውን በመልካም ሰማዕትነትና መንፈሳዊ ገድል ከፈጸሙት ውስጥ፣ ቍጥራ ቸውን ያወቅነው የቅዱስ ብፁዐዊ እስጢፋኖስ ወንድና ሴት ልጆች ሰማዕታትና ጻድቃን ጠቅላላ ድምር ፲፻፬ (1004) ነው። የማናውቀውን እሱ [እግዚአብሔር?] ንብረቱን ይሰብስብ።…”[10]

እኒህ ሁሉ ክርስቲያኖች ንጉሡ የቍጣና የአምልኮ ባዕድ እሳት የተበሉት ከሕያው እግዚአብሔር በቀር ለማርያም ሥዕልና ለመስቀል ምልክት አንሰግድም በማለታቸው ነበር።[11] ይህን አይተን፣ መስቀሉን ሰቀሉት ቢባል ታዲያ ምን ይገርማል?

ጌታ የመሰቀሉ ነገር ገና በማንም ልብ ባልታሰበበት ጊዜ “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል” (ማቴ.1038) ሲል በእዉኑ ስለየትኛው መስቀል ለመናገር ፈልጎ ይሆን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሕይወት ብቻ የምንመስለው አይደለንም፤ ለወንጌሉ እውነት በሞቱም እንኳ የምንተባበር ነን እንጂ (ሮሜ. 65)የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን” (2 ቆሮ. 410 ) ተብሏል። ከእርሱ ጋር ለመኖር ከሕይወቱ ጋር እንደምንተባበር ሁሉ ከሞቱም ጋር በጥምቀት አነድ ኾነናልና መስቀሉን (መከራና ሞቱን ችግርና ስደቱን ) ተሸክመን በመከተል ለእርሱ እንድንኖር ተጠርተናል። ይህሞቱን በሥጋችን የመሸከምጥሪ የተመሳቀለ እንጨትና ብረት ከመሸከም ጋር ካጣመርነው ግን መስቀሉን ሰቀልነዋል ማለት ነው። መስቀሉ የፋሽን ቍስ አይደለም እኮ!

መስቀል በታሪከ ድነት ውስጥ ከነበረው ቦታ የተነሣ የክርስትና እምነት ምልክትና አርማ ተደርጎ መወሰዱ ባያስገርምምመስቀሉ በራሱ የተለየ መድኀኒትነት እንዳለው ማሰብና ማስተማር ግን ትክክል አይደለም። በወርቅ በከበረ ድንጋይ፣ ከእንጨትና በሌሎችም ነገሮች አስመስለን በሠራናቸው የመስቀል ምልክቶች ለመዳን መሞከር መጽሐፍ ቅዱሳዊነት የለውም።

የተመሳቀለ የመስቀል ምልክት ያለውን ግዑዝ ነገር በሰሌዳ፣ በመጽሐፍ፣ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በተንቀሳቃሽም ኾነ ቋሚ ነገሮች ላይ ማዋል የነበረና ያለ ነገር ነው። በጌጣ ጌጥ መልክ አሠርቶ በተለያየ የአካል ክፍል ላይ ማንጠልጠል ወይም ደግሞ መነቀስም የተለመደ ኾኖ ቈይቷል። ይህ ሁሉ ኾኖ ግን፣ ሕይወታችን ለተሰቀለውና ከሙታን ለተነሣው ጌታ ያልተሰጠ፣ እናምነዋለን ለምንለው ወንጌል ሕይወታችን የማይኖር ሰዎች፣ ደግሞም ለዐዲስ ልደት በሚኾን መታጠብና በመንፈስ መታደስ ሳንጐበኝ በኀጢአታችንና በበደላችን ምክንያት በሞት ሰንሰለት እንደ ታሰርን መስቀል ብናንጠለጥልሰቀልነውቢባል እንጂ ሌላ ምን ፋይዳ አለው? ስመ ክርስትናን አንግበን መስቀሉንም አንጠልጥለን ሕይወታችን ግን ለክርስቶስ ለራሱ ያልተሰጠ ከኾነመስቀሉን ሰቀሉትመባላችን ተገቢ ይኾናል።

ድርጊታችን የሚያሳየው ግን ከታሪካዊ ስሕተታችን መታረምን ሳይኾን ወደባሰው መስረግን እንደ መረጥን ነው። የሀገሬ ሰውየባሳ አታምጣየሚለው ወዶ አይደለም። በመስከረም 2006 .. በአቃቂ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መስቀል ከሰማይ ወረደ መባሉንና በሺህዎች የሚቈጠሩ ምዕመናንበነጐድጓድና በብርሃን ታጅቦ ከሰማይ የወረደውን መስቀልለማየት እየጐረፉ መኾናቸውን አዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል። ይህ መቼም እጅግ አሳዛኝ ነው። ጴጥሮስ ከሰማይ የወረደውና ወደ ሰማይ የወጣው አንድ ጌታ እርሱም ኢየሱስን እንድናስብ ሲመክረንዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት” (1ጴጥ. 315) የተባልን እኛ፣ ገና ከሰማይ ስለሚወርድ የመስቀል ምልክት እናንጋጥጥን? ምን ያለ አለማስተዋል ነው?

ደግሞ በሌላ መንገድ መስቀሉን የሚሰቅሉ ሸቃጮች አሉ። ይህም አንዳንዶች እንደሚጠቀሙበት አጠራር በእነእንደልቡ ቤትየሚገነግኑትእነጎበዜየሚሠሩትን ይመለከታል። እነዚህም ሰዎች ፕሮቴስታንታዊ ትውፊቱን ተገን አድርገው የክርስቶስን ማኅበር በመከፋፈል የታላቁን ጌታ ስሙን፣ ክብርና ዝናውን ጋርደው የራሳቸውን ገድል ሲተርኩ የሚውሉመስቀል ጋራጆችናቸው። እነዚህም መስቀሉን ሰቅለዋል ቢባል ትክክል ከመኾን አይጎድልም።

እንደሚታወቀው፣ ታሪካችንና ባሕላችን በአመራር ጠቅላይነትተጠምቆ የደቆነበመኾኑና ይህንኑ እርሾ ይዘን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስለ መጣን፣ ያው ተመሳሳይ አባዜአችንሳያቀስ ላይለቀንየዘመተብን ይመስላል። ስለኾነም፣ ቤተ ክርስቲያንኀላፊነቱ ያልተወሰነ የግል ማኅበርትመስል በግለ ሰቦች ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሥር የተንበረከከችበት አያሌ አስረጅዎች ሞልተዋል። በትንንሽ ኲርፊያና አለመግባባት የተነሣ አባላት ሲበተኑና ሲታወኩ የምንመለከትበት ጊዜ ላይ ነን። መስቀሉን የተሸከመ ሎሌ የእግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢ  (1 ቆሮ. 41-2) ሳይኾን፣ ማዕከልነቱን ማስጠበቅ በቻለው ግለሰብ ቀጥተኛ የባለቤትነት መሥመር ተላሚነት ላይ መንጠልጠላቸውም በሰፊው ይታያል።

አሁን አሁንማ ከዘመናችን ስብከቶች፣ ትምህርቶችና ዝማሬዎች ውስጥ የመስቀሉን መልእክት ምን ሰወረው?” የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ኾኗል፤ ልንቆጭበትም የተገባ ነው። በየጉባኤው የተዘሩት አንዳንድ ሰባኪያን፣ መምህራንና ዘማርያን ሕግን ያለ ጸጋ፣ የሥነ ሥርዓት ርምጃን ከተሓድሶ ውጭ ይሰብካሉ። ግለሰባዊ ድነትን ከማኅበራዊ ርኅራኄ ነጥለው ያመነዥካሉ። ፍቅር በጐደለው ሃይማኖት መመሪያዎችን እንደዶፍ ያዘንባሉ። የመስቀሉን ጥበብ ሸፍነው ዕውቀታቸውን ይደሰኩራሉ። የመሲሑን ግርማ ገፍትረው የራሳቸውን ገድል ይዘምራሉ። ሌሎች ዝነኞች በፈንታቸው ክርስቶስ ስምሰበብ ጐረቤቶቻቸውን ተንኵሰውና አዳቅቀው ሲያበቁ በኩራት ይፍነከነካሉ። ተቃውሞ ከገጠማቸውም ራሳቸውን እንደ ሰማዕት ይቈጥራሉ። ለመኾኑ የራሳችንን ስምና ዝና ከፍ አድርገን ያኖርነው መስቀሉን ወዴት ሰቅለነው ነው?!

ይህ ሐዋርያዊ ድምፅ እንዴት እንደማያቃጭልብን ግራ የሚያጋባ ነው።በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና” (1 ቆሮ. 22) እኛስ ምን ለማወቅና ምን እንዳወቅን ለማሳወቅ ነው ዛሬ በጽኑ የዘመትነው? ምንነቱ የማይታወቅ ሐሳብ እያንበለበልን መንጋውን በማጯጯህ ላይ የተመሠረተመንግሥተ እኔ የማቆም የጥቅመ ሰናኦር መንፈስ እየከበበን ይኾን (ዘፍ. 11)?

በሌላ በኩል ደግሞ በትኵረት ስንታይ የመስቀሉን ክብር እንፈልጋለን፤ ውርደቱን ግን እንሸሸዋለን። ምነው? ባለግርማው መሲሕሥቅዩው ሎሌአልነበርምን? ወንጌሉ ትበለጽጋለህ የሚል መልእክት ብቻ ተሸከመ ይመስል ስሙን ሳይቀር ቀይረውየብልጽግና ወንጌልይዘው የመጡ ወንጀል ሰባኪዎች መስቀሉን ሰቀሉት ሊባል አይገባ ይኾን? እንጀራና ሆድ ይህን ያህል ዋነኛ ነገር ኾነው መድረኩን ሲወሩ፣ ወዛቸውን የጠረጉበትን ለስላሳ ወረቀት ሳይቀር በገንዘብ የሚሸጡ ነጋዲያን በወንጌል አገልጋይነት ስም ሲወራጩ ባየን ጊዜ መስቀሉን ሰቀሉት ብለን እንጮኻለን።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሼፈርድ ቡሽሪ የተባሉ ግለሰብ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት የታየው ዕብደት ለአስረጂነት እዚህ መጠቀስ ይኖርበታል። በነጻ የተሰጠው የክርስቶስ ጸጋና የመስቀሉ ሥራ ገብቶኛል እያለ በሚመካ ማኅበረ ሰብ መካከል አንድ ነጋዴየፈውስ ዘይትእናየበረከት ጸበልበጠርሙስ እያሸገ ሲቸበችብ ዝም ከተባለ፣መስቀሉን ሰቀሉት አይባልምን? “ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉ የክርስቶስንም አይደለም” (ፊል. 221) እያለ ጳውሎስ ያለቀሰው[12]የመስቀሉ ጠላቶችኾነው ስለሚመላለሱቱውሾችአይደለምን (ፊል. 32) መታወቂያቸውስ የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለውመሸቃቀጥ መኾኑ አልተጻፈምን (2 ቆሮ. 217)? “እጄ አብረቀረቀየሚል ሰው በውኑ የብርሃን መልአክ የመሰለ አንዳች ፍጡር (2ቆሮ. 1114-15)[13] ቢመለከት ምን ሊውጠው ነበር? “መላእክት ቢኾኑ፣ ልዩ ፍጥረት ቢኾን፣ ያለውና የሚመጣው ቢኾን፣ ኀይላት፣ ከፍታና ድንቆችእንኳ ቢኾን ከክርስቶስ ፍቅር እንደማይለይ አልተጻፈምን (ሮሜ 837-39)? በውኑ ይህእግዚአብሔር መምሰል ማትረፊያ በሚመስላቸው ሰዎቸ ዘንድየማይጠፋ (1 ጢሞ. 64-5) ስግብግብነት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ስም ተመስሎ አደባባይ ሲወጣ ማየት ነውር አይደለምን? ኧረ፣ መስቀሉን ሰቀሉት!

አንዳንዶቻችን ደግሞ በተገላቢጦሽ ይቅርታን ከመስቀሉ ውጭ እናውጃለን። ኅብረትን ያለ ጸጋና ተግሣጽ እናልማለን። ንጉሡን ገፍትረን መንግሥቱን ልንሰብክ እንቃዣለን። ምትክ የለሽ የኾነውን ወንጌል በአርቲ ቡርቲ ተክተን እየተጯጯህን ሰዎችን ለንስሐ እንጋብዛለን። እግዚአብሔርን ማሳዘዘናችን ግድ ሳይለን ሰዎች እንዳይከፋቸውና ከስብሰባችን እንዳይቀሩብን እንጠነቀቃለን። መንፈስና ኀይልን በመግለጥ የመስቀሉን ቃል ማወጅ ስላቃተን፣ ወጣቶቻችን እንዳያኮርፉ እናቈላምጣቸዋለን። ኧረ መስቀሉ ቃል ወዴት ነው? የሰቀላችሁትን መስቀል አውርዱት እንጂ!  

ወንጌል የሰዎችን ሓሳብ እያንኰታኰተ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ያገንናል። ለሚያምኑ ሁሉ ለማዳን የእግዚአብሔር ኀይል ነውና (ሮሜ. 117) የመስቀሉ ቃል ለብዙዎችሞኝነትሲኾንባቸው፣ ለበርካቶችማሰናከያነው፣ ለጥቂቶች ግንየእግዚአብሔር ጥበብና ኀይል ነው” (1 ቆሮ. 118) ይህን እንዴት እንዘነጋለን? ይህ እውነት ችላ ከተባለስ ለተከታዩ ትውልድ ምን እናስተላልፋለን?

መደምደሚያ


ከሁሉ አስቀድመን የወንጌልን መልእክት ጭብጥ እናስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል። ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ” (1 ቆሮ. 151-3)። ከዚህ ውጭ የኾነ መልእክት በምንም መንገድ የእግዚአብሔር ወንጌል ሊኾን አይችልም።

ቀጥሎ ደግሞ ይህን እንገንዘብ። የእግዚአብሔር ሕግን መተላለፋችን የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን በማፍሰስ ተቤዥቶናል። ይህን ለማድረግም በመስቀል ላይ ሞቶልናል። ስለዚህ ሕይወታችን ከመስቀሉ አንጻር የት እንዳለ እንፈትሽ። በኀጢአተኛነትና በበደል የታሠርን ኾነን፣ ነገር ግን ንስሐ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር ገና ላልተስማማን ወገኖች፣ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን” (2 ቆሮ. 520)

ደግሞም አንድ እንጨምር። ይህች ሀገር ከክርስትና ጋር በተቆራኘው የረጅም ዘመን ታሪኳ ምክንያት የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ክብረ በዓል በብሔራዊ በዓልነት የሚታሰብባት ኾናለች። ይህ በመኾኑ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ነገር ግን የዚህ ጊዜ ዐቢይ ነገር መብልና መጠጥ አይደለም።የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና” (ሮሜ. 1417) የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤን በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ አስበን ስናበቃ ወደየምውት ሥራችን የምንመለስበት በዓለ ንግሥ አይደለም። መጽሐፍ እንደሚል የፋሲካችን ፋይዳው ግልጽ ነው።ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም”(1 ቆሮ. 57-8)


“የመስቀሉን ክብር ካልያዝን፣ ሕይወታችን መቅኖ ቢስ ኾኖ (ባክኖ) ቀርቷል ማለት ነው። እንደ ውድ መዝገብነቱ (ሀብትነቱ) ደስ ተሰኝበት፤ ከየትኛውም ደስታ በላይ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው እንደመኾኑ ተጠጋው። በማንኛውም ህማምህ ጊዜ ደስታን ቅዳበት፤ በአንድ ወቅት ለኛ ለሰዎች ሞኝነት ይመስለን የነበረው የአምላክ መስቀል ጥበባችን፣ ኀይላችንና በዚህ ዓለም የቀረን ብቸኛው ትምክሕታችን መኾን አለበት።”

ጆን ፓይፐር፣ Don’t Waste Your Life


ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ዘአፈጸመኒ በደኅና።

መልካም የስቅለትና የትንሣኤ ክብረ በዓል ይሁንላችሁ።






[1] ኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ሃይማኖተ አበውዘጎርጎርዮስ ፣ ም. 36፣ ቊ. 12 (ዐዲስ አበባ፦ ትንሳኤ ማተሚያ ድርጅት፣ 1986) 124።
[2] J.D Douglas and Merrill C. Tenney. (eds.), New International Bible Diction- ary (Grand Rapids: Zondervan, 1987), p., 241.
[3] አባ ጎርጎርዮስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ (አዲስ አበባ፤ አልቦ አሳታ ሚ፣ 1991 .) ገጽ፣ 104
[4] ኮሊን ማንሰል (ቄስ) ትምህርተ ክርስቶስ (አዲስ አበባ፤ 1999 .) ገጽ፣ 334
[5] የኢ....ክ፣ ሃይማኖተ አበው፣ ዘኤጲፋንዮስ፣ ምዕ.. 57 . 9 . 18 (አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ 1986) 192
[6] መሠረት ስብሐት ለአብ፣ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ  (አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ 1951 .) ገጽ፣ 109-110፡፡
[7] በነገራችን ላይክሩሴድ መሠረታዊ ትርጓሜው አንድን ነገር ለማስተዋወቅ ወይም ሊወገድ የሚገባውን አላስፈላጊ ነገር ለማጽዳት በጋራ የሚደረግ ጫን ያለ ዘመቻ ተኰር እንቅስቃሴ ነው። ነገር ግን፣ ይህ ሥያሜ በታሪክ የሚታወሰው፣ 11ኛው እስከ 13ኛው ምእት ዓመት  በነበሩ ዘመናት የአውሮጳ ስመ ክርስቲያኖች “‘ቅድስት ምድርንከአሕዛብ መዳፍ (ቊጥጥር) ነጻ ለማውጣትበሚል -ክርስቲያናዊ መርሕ 200 ዓመታት ያህል ያካሄዱት ተከታታይ የጦር ዘመቻ ነው።
[8] መስተበቊዕ ዘመስቀል
[9] ኢኦተቤክ. ተአምረ ማርያም (አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ 1985 .) ገጽ፣ 133-134
[10] ጌታቸው ኃይሌ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስበሕግ አምላክ (ሚኖሶታ፤ ኮሌጅቪል፣ 1996) ገጽ፣ 220-221፡፡
[11] ኢኦተቤክ. ተአምረ ማርያም (አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ 1985 .) 133፡፡
[12] ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ” (ፊል. 3፥18)
[13] “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል” (2 ቆሮ. 11፥14)።