-->
ዛቲ ጦማር
ዛቲ ጦማር
ይህን ለሚያነብቡ ኹሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላም ይሁን!!
እንኳን ለዐዲሱ ዘመን በሰላም አደረሳችሁ (በዚህ አባባል “አድራሽ” መኖሩን ልብ ይሏል)! ያው እንደምታስታውሱት፣
ይህ የኔና የናንተ አገር፣ “ለዐዲሱ ዓመት እንኳን ደረሳችሁ!” በማለት በከንቱ የሚጓደዱ ካኪ ለባሽ
ባለጊዜዎችን በየሚዲያው አስተናግዶ ያውቃል፡፡ ይህን ጕድ ዐይን ዐይታለች ጆሮም ሰምታለች፡፡ ሰውን ማዕከል ባደረገ ፍልስምና የልቦናው ትሕትና ተመጦ፣ “ተፈጥሮን በቊጥጥር ስር ለማድረግ” እንደሚቻለው በእውን ቅዠቱ የወሰነ ድኩም ፍጡር “አድራሽ” እንደማይሻ እኒያ ወገኖች አምነው (በእነርሱ አበባል “አረጋግጠው”) ነበርና! ስለዚህ፣ እንዲህ ያለው ምስኪን ፍጡር፣ በገዛ አቅሜ እና በዲያሌክቲካዊ ሒደት መርሕ ራሴው በራሴ “ደራሽ” ነኝ እያለ ይቃትት ዘንድ አልታከተም ነበር፡፡ ርግጥ ዛሬም የዚህ ልክፍት “ሰለባ” የኾኑ ወገኖች ከመካከላችን አልታጡም፡፡ እነሆ፣ ሁሉ ነገራቸው “እኔ፣ ለእኔና በእኔ” እንደተለወሰ አለ፡፡ ከገጣሚ አበባው መላኩ ስንኝ ልዋስና (እርሱ የጻፈው ስለሌላ ጕዳይ መኾኑ ሳይዘነጋ) እንዲህ ዐይነቱ ወገኔ፣ “…በከንቱ ድግግ ጠባይ የኩርማን ልቡን ወጥሮ” እንደተባለው የኾነበት ይመስለኛል፡፡
ለማንኛውም “አድራሽ” አለ!
ሁሉ ከእርሱ፣ ሁሉ በእርሱ፣ ሁሉ ደግሞ ለእርሱ የኾነ ሉዓላዊ “አድራሽ” መኖሩን ማወቅ ምንኛ መታደል ነው! ለማንኛውም ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ እንኳን አደረሳችሁ ብያለሁ!! መጪው ዘመን ለእውነት የምንኖርበት፣ ከእውነትም በሚገኘው ነፃነት ሐሴት እያደረግን የምንመላለስበት እንዲኾን ልባዊ ጸሎቴ ነው፡፡ ርግጥ ነው እንደተለመደው፣ “ምኞቴ ነው” አላልኩም፡፡ “ምኞቴ ነው” ያላልኩት ይህ እንዲፈጸምልን ሳልመኝ ቀርቼ ሳይኾን፣ ምኞት ብቻውን ምን ይፈይዳል ብዬ ነው፡፡ የጸሎት ሰው ባልኾንም እንኳ፣ ከመመኘት ይልቅ በጥቂቱም ቢኾን ብጸልይ ይሻላል አይደል? ጸሎትን የሚሰማ አምላክ በሰማይ አለና (መዝ ፷፭÷፪)፡፡ አቤት የኔ ነገር! ገና ሰላምታዬን ሳላጠናቅቅ ሁለት አንቀጽ ተገባደደ! “የቃላት ምጣኔ” ምናምን የሚባለው ነገር “ድቤ በላ” በሉኛ! እናም በዚችው ሹልክ ብዬ ሰላምታዬን ላጠናቅቅ—“ሻሎም”!
ከሰላምታዬ በመለጠቅ ወደ ዋነኛ ሓሳቤ ባዘግምስ? ይህም ዋነኛ ሐሳብ በዚህ ጡመራ (Blogging) መጀመር ምክንያት የሚፈጠረውን የእኔንና የናንተን ትስስር ይመለከታል፡፡ ግን ይኼ “ይመለከታል” ብሎ ነገር ምንድነው? ማመልከቻ የምጽፍ አስመሰልኩት አይደል? ልሰርዘው መሰል፡፡ ርግጥ መሰረዝ እችል ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳልሰረዝኩት እንድታውቁ ስል ትቼዋለሁ፡፡ ለማንኛውም ይህን በዚህ ትቼ ወደ ፍሬ ነገሩ ልግባ፡፡ ከላይ በርእሱ ለመጥቀስ እንደተሞከረው… የባሰው መጣ!!...
ከዚህ በኋላስ የምር ነው፡፡ እኔ ወንድማችሁ ወይም ልጃችሁ ሰሎሞን ጡመራ ጀምሬአለሁ፡፡ ስለዚህ….ይቺ ደግሞ ልምምጥ ትመስላለች፡፡ አይ እንግዲህ! ታዲያ ምን ብዬ ልጀምር ነው? እርግጥ የሚከተለው ምርጥ ሳይኾን አይቀርም፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድና በሕይወት ብኖር፣ በሚመጡት ዘመናት ከቃለ እግዚአብሔር የተማርሁትን እና የምማረውን፣ ካደግሁበትና ከምኖርበት ማኅበረ ሰብ የቀሰምኩትንና የምቀስመውን፣ እንዲሁም፣ በትምህርት ቤትም ይሁን ከዛ ውጭ ከነበሩትና ካሉት መምህሮቼ ያካበትኩትንና ገናም በሒደት የማገኘውን እውነት አንድ ላይ በማዛነቅ በተለያዩ ርእሰ ጕዳዮች ላይ ያሉኝን ምልከታዎች ለማስነበብ እንድችል በክርስቶስ ጸጋ እጀምረው ዘንድ እነኾ መጦመሪያዬን ወጥሬአለሁ፡፡ እፎይ! ይህ ደግሞ የዐረፍተ ነገር አወቃቀርን የሚደነግጉ ሰዋስዋዊ መርሖዎችን ሳይጥስ አልቀረም መሰለኝ፡፡ በዚህ የሞኝ ጅራፍ የሚያህል ዐረፍተ ነገር ውስጥ ሰዋስዋዊ ዝንፈት ከሌለማ ጕድ ነው! “ግራም ነፈሰ ቀኝ” ጡመራ መጀመሬን ለናንተ ለማብሠር ያደረግሁትን ሙከራ ተረድታችኋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እና የጡመራ ሓሳቡን እንዴት አያችሁት? አሰተያየት ብጤ ሰንዝሩ.. እ!
በርግጥ ይህን ነገር ስጀምረው የሚያነበኝ እንደማላጣ በቂ “ግምት” ይዤ ነው፡፡ ይህም ግምቴ ከሁለት ምክንያቶች ይመዘዛል፡፡ አንደኛው፣ ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ መግቦት አኳያ የሚታይ ነው፡፡ እርሱ፣ ቸሩ ጌታ፣ አንድም ፈጥሮኝ (መዝ. ፻፴፱÷፭-፮)፣ ሁለትም እንደገና ፈጥሮኝ (ኤፌ ፪÷፲) ሲያበቃ፣ በእናንተ መኻከል ባዶዬን እንከወከው ዘንድ አልሰደደኝም ብዬ አምናለሁ፡፡ እርሱ ለዘሪ ዘርን ለበላተኛም መብልን ይሰጥ የለምን? “ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል” (፪ኛ ቆሮ ፱÷፲) ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ስለኾነም፣ በዚህ የተንጣለለ የማኅበረ ሰብ ሁዳድ መኻል (ለሌላው
የሚያካፍለው ሰማያዊ ስጦታ እንደሌለው ብጤ) በከንቱ አያንከላውሰኝም ማለት
ነው፡፡ እርሱ ባለጸጋ ነዋ! ይህ ዋነኛ ትምክህቴ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ አንባቢ
ወዳጆቼን ይመለከታል፡፡ እናንተን
ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጨባጭ ማስረጃ አለኝ፡፡ ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች ሞነጫጭሬ የወረወርኩትን የጽሑፍ “ጭብጦ” ሳይንቁ ገምጠው አስተያየቶቻቸውን የሰነዘሩ ወገኖች ዙሪያዬን ከበውኛላ! አስተያየታቸው ደግሞ “ጨምርና ጻፍ” የሚል ማትጊያም ነበረው፡፡ ታዲያ እንዴት አልነበብም?
የኾነ ኾኖ መወራረዳችን አይቀሬ ነው፡፡ ውርርዱም፣ “እኔ እኾን ከመጻፍ የምሰንፈው? ወይስ እናንተ ናችሁ ከማንበብ የምትናጠቡት?” የሚል ነው፡፡ በርግጥ አንዳች ጠቃሚ ነገር ጠብ የማይልበት፣ ቊም ነገር የማይገኝበትና እንጨት እንጨት የሚል የፊደል ግሳንግስ “በለጠፍኩ” ጊዜ ሁሉ (በርግጥ የማደርገው አይመስለኝም)፣ “እያቃራችሁም ቢኾን” የማንበብ ግዴታ ያለባችሁ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ያኔም እንኳ ያለማንበባችሁን ምክንያት “በጨዋ ደንብ” እቅጯን ትነግሩኛላችሁ እንጂ ሹልክ ብሎ መጥፋት አይፈቀድም፡፡ እንደዛ “ውኃ የማያነሣ” ችኮ ነገር የገጠማችሁ እንደኾነ፣ “ነገርህ እንጨት እንጨት ስላለኝ ነው” ትላላችሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡
እኔም በተቻለኝ ሁሉ ከጡመራው ገጽ እናንተን በሚመጥን ሓሳብ መጠን ተሞልቼ ላለመጥፋት እጥራለሁ፡፡
በሌላ በኵል፣ ይህ ጡመራ ሙከራ መኾኑንንም ትገነዘቡልኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እዚህ ሙከራ ውስጥ የገባሁት “ያገኘውን የወረወረ፣ ፈሪ አይባልም” ብዬ ነው፡፡ ወደ ሰፊው ባሕር የምወረውረውና የባሕሩን ውኃ የማምቦጫርቅበት “አሳር የሚያህል ናዳ” ባይኖረኝም እንኳን፣ በትንንሽ ጠጠሮች ጥብጠባዬ የሚፈጠሩትን የውኃ ላይ ቀለበቶች በትዕግስት እያየን እንደመም እንደኾንስ ማን ያውቃል? አንድዬ ምን ይሣነዋል? ያው ጋንስ በጠጠር ይደገፍ የለ? ለካ ዳዊትም “የዘመተው” በጠጠር ኖሯል! ወይ የጠጠር ነገር! ጠጣር ይሁን እንጂ “ጠጠር” ዋዛ አይደለም፡፡
በተረፈ በምጫጭረው ሓሳብ ላይ ያላችሁን አስተያየት እንደምትለግሱኝ እተማመናለሁ፡፡ ብዙ ቃል ባለበት በዚያ ስሕተት አይጠፋምና፣ በጡመራው ሜዳ ልጓም እንደሌለው… እንዳልኾን ምከሩኝ፤ አልፎ ተርፎም በማትስማሙበት አስተሳሰቦቼ አንጻር ሞግቱኝ፡፡ ብረት ብረትን እንዲስል እንዲሁ ባልንጀራም ባልንጀራውን እንደሚስለው ንጉሥ ሰሎሞን ተናግሯል አይደል! በተቀረው፣ በጸሎታቸሁ እንድሰጥ ልባዊ ልመናዬ ነው፡፡ በዚህ ተግባር ከጸጋው ድጋፍ በቀር ሩቅ መጓዝ እንደ እልም ነውና፡፡ የሚያሳድግ አምላክ ይርዳኝ እንጂ “ነበር” ተብሎ መዘከርስ አለ አይደለም ወይ?
ወደ
እግዚአብሔር አምላካችንም እንዲህ እላለሁ፣ “አቤቱ፥ ምሕረትህን ለዘላለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ። እንዲህ ብለሃልና፡- ምሕረት ለዘላለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል” (መዝ ፹፱÷፩-፪)፡፡ እውነተኛው አምላክ (ዮሐ ፲፯÷፫) ለእውነት መኖርን ያብዛልን፡፡ መልካም ዐዲስ
ዓመት!!
ወንድሜ ሰለሞን
ReplyDeleteጦማርህን በማግኘቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ምልከታዎችህን ለማንበብ ከሚተጉት አንዱ እሆናለሁ ብዬ አምናለሁ።
በነገር ሁሉ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን!
ወዳጅህ
ጆን
በርታ! ሁሉን ቻይ አምላክ ይረዳህ!!
ReplyDeleteመልካም አዲስ ዓመት፡፡
ወዳጄ ሶል.....ይህን ጦማር መጀመርክ በጣም ነው ያስደሰተኝ:: በዚህ ጦማርም ለሚቀጥሉት ግዚያቶች ያንተን ምልከታዎች ልታስነብበን ቆርጠክ ስለተነሳክ እኔም ይህንኑ ያንተን ምልከታዎች ለማንበብ ቆርጭያለው:: (ምንድን ነው ቆርጠክ፣ ቆርጭያለው የሚሉት ቃል? የሆነ የጦርነት ነጋሪት ጉሸማና የጥሬ ስጋ መብላት ውድድር አስመሰልኩት እኮ!) ስለዚህ ውርርድ ጀምረናል ማለት ነው:: አንተ ለመጻፍ እኔ ለማንበብ....አንተ በመጻፍ ትዝል ይሆን እኔ ከማንበብ እቦዝን እሆን? ምን ለማለት ነበር ከላይ ያለው ይህ ሁሉ የቃላት ግሳንግስ? አዎ!! በርታ ጎብዝ ፃፍ እኛም እናነባለን ልል አስቢ ነው::
ReplyDeleteእግዚያብሄር በነገር ሁሉ ይርዳክ::
ያሬድ!
"እየጣፈጥዎት ጀምረው እየጣፈጥዎት ያልቃል!" … ነበር ያሉት እነዚያ የማስታወቂያ ሰዎች? ዛሬ ይህንን አባባል በሚገባው ቦታ ብጠቀመው የሚቀየሙኝ አይመስለኝም!!
ReplyDeleteሶል ወዳጄ ጌታ ይባርክህ!! ብዕርህም ቀለም ከመትፋት አትደከም!
ፀጋ
ሶል፡
ReplyDeleteእኛ የማናውቀው አማርኛ አለ ወይ ሶል? በተቻለህ መጠን አማርኛውን አቅልለው እንደኔ የሉ ማንበብ እንዲችሉ፡፡ እንዲህ ካሎነ ዘንዳ መፋታታችን ነው፡፡
ውድ ሶል
ReplyDeleteእንደ እውነቱ ከኾነ ጅማሬህ እጅግ በጣም ግሩም ነው። ጌታ ጥረትህን ይባርክ! ኾኖም ግን አንዳንድ ወዳጆችህ ሊነግሩህ እንደሞከሩት አንዳንድ በጽሁፍህ ውስጥ የምትጠቀማቸው ቃላቶች ለብዙዎች መክበዳቸው አይቀሬ በመኾኑ ብታስብበት መልካም ይኾናል።
እንደ እኔ፣ እንደ ኔ ከኾነ ጭራሽ እንዲህ አይነት ቃላቶችን አትጠቀም ማለቴ ሳይኾን ለእንዲህ አይነት እንግዳ ለሚመስሉ ቃላት ከስር የግርጌ ማስታወሻ ላይ ትርጉማቸው ቢሰፍርልን የሚል አስተያየት አለኝ። ይህንን የምለውም እንደዚህ አይነት ትርጉማቸው አብሮ የሰፈረላቸውን ቃላቶች ለመማርም ጭምር እድሉን እንድናገኝ በማሰብ ነው፤
በድጋሚ እግዚአብሔር ይባርክህ!