Monday, April 20, 2020

ችንካሩማ እኔው ነኝ! I AM THE NAIL



ችንሩማ እኔው ነኝ!

"ልደቱ ጨለማውን አስደንግጧል። ሕይወቱ አጠያይቋል፤ ትምህርቱ አወዛግቧል። በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ በኀጢአት ላይ የተመሠረተው የሰው አገዛዝ በዚህ ብርሃን መጋለጡ የሚጠበቅ ነበርና አንጃ ግራንጃው ብዙ ኾነ። 


የመንግሥተ እግዚአብሔር መገለጥ በክርስቶስ ማንነትና ትምህርት በኩል ወደ ዓለም ሲገባ የጨለማው ሥልጣን መንኰታኰቱ አልቀረለትም። ፍትሕና ጽድቅ በተጓደለበት የአዳም ሥርዐት ላይ ብርክ የሚያዘንብ የታሪክ ባለቤትና ጌታ በማዳኑ ብርሃን ሲገለጥ፥ ክፉው እንዴት አይደናገጥ?!
.
እንጂማ፥ እርሱ የማንንም ሕይወት አልጐዳም ነበር፤ በዘረፋና ምርኮ አልተሳተፈም፤ ሥዒረ-መንግሥት አላካኼደም፤ ለድኾች ወዳጅ፥ ማኅበራዊ ስብራት ወደ ጠርዝ ለገፋቸው ምንዱባን ጓደኛቸው ነበር። እረኛ እንደሌለው መንጋ ለተበተኑት ሕዝብ በርኅራኄ ያዝናል። የተራቡትን መግቧል። የተጠቁትን ነጻ አውጥቷል። የታሰሩትን ፈትቶ፥ የተበተኑትን ሰብስቧል (ሉቃ. 4፥17-19)። “ኹሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል” (ማር 7፥37)።
.
ሰው ግን ውለታውን የከፈለው በተገላቢጦሽ ኾነ። ኹሉን የያዘና የሰውን ሕይወት እርቃን በጸጋው የሚሸፍን የሕይወት ራስ ሰውን ፍለጋ በመጣ ጊዜ ዓለም ለእርሱ ቦታ አልነበራትም። ሕይወታችንን በሚመስል ምጸት ዓለም ለኢየሱስ ያቀረበችለት ቦታ በረትና ግርግም ብቻ ነበር (ሉቃ. 2፥7፡ 12፡ 16)፤ ያውም የተውሶ ግርግም። ለማስተማር ታንኳ ተውሶ ነበር (ሉቃ. 5፥3)፤ ንጉሣዊ አገባቡን የሚያረጋግጠው የኢየሩሳሌም ጕዞው በተውሶ አህያ ጀርባ ላይ በመቀመጥ ኾነ (ማቴ 22፥ 1-16)። የመጨረሻውን የፋሲካ ራት በተውሶ ቤት አበላ (ሉቃ. 22፥7-12)። በመጨረሻም የሰው ልጅ ለመሲሑ ያዘጋጀው “ከፍታ” የመስቀል እንጨት ኾነ፤ በዘረጋው የፍቅር እጁ ላይም ችንካር አኖረበት። ንፉጉ ዓለም፥ ክፉውም የሰው ልብ የእግዚአብሔርን መሲሕ በጭካኔ ሰቀለ። ሊቤዠው የወረደለትና የተዋረደለትን መሲሕ በክፋት ገደለ፤ ቀበረም። የተቀበረውም በተውሶ መቃብር ነበረ (ማቴ. 27፥60)።" ("የተቈረሱ ነፍሶች"፥ 236-7) አያችሁ፤ የዚያ ዘመን ሕዝብ ንቅል ብሎ ወጥቶ መድኅኑን በመንጋ ገደለ፤ ሰቀለ።
.
ያንን መሲሕ ገዳይ መንጋ የትውልድ ተራ ተርታችንን ጠብቀን በታሪክም በትምህርትም ስንወቅሰው፥ በምሳሌና በፈሊጥም ስንቀጠቅጠው ኖረናል። በርግጥ ሲወቀስና ሲነቀፍ መኖሩ ገና ይቀጥላል። ነገር ግን፥ እኔ በመካከላቸው ኖሬ ብኾን ምን አደርግ ነበር? ከሰቃዮቹ ወይም ከአሠቃዮቹ ላለመኾኔ ማረጋገጫ የሚኾነኝ ቅንጣት ምስክር አላገኝም። የተጣራና የተረጋገጠ ማስረጃ ግን አለኝ። መሲሑ ኢየሱስን የሰቀለው የኔ ኀጢአት ነው። "እርሱ ስለመተላለፋችን ተወጋ፤ ስለበደላችንም ደቀቀ" (ኢሳ. 53፥5ዐመት) አልተባለምን? አያችሁ፤ ችንካሩ እኔው ነበርሁ። በደሌ ነበር ያደቀቀው። ጌታዬ ከላይ መጥቶ በመስቀል ላይ የተሰበረው ለእኔ ኀጢአት ሲኾን፥ የሰበርሁት እኔው ነበርሁ። አንተና አንቺ ናችሁ ብዬም እገምታለሁ። የእኔ ግን ርግጥ ነው፤ ችንካሩ እኔው ነበርሁ፤ ነኝም።

No comments:

Post a Comment