በስሜት ስንከንፍ እውነትን እንዳንገድፍ
ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!!
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት ቈይታ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በመመለሷ ኢትዮጳውያን ፈንድቀዋል። በርግጥ፥ ባይፈነድቊ ነበር የሚገርመው። “የበይ ተመልካች” ብቻ መኾን ማን ይፈልጋል? ሌሎች “ሲበሉ” አብሮ መደሰት አስፈላጊ ቢኾንም፣ ከዓመት-ዓመት እያፋሸጉ (እያዛጉ) “ገበታውን” እና “በይዎቹን” በፎቶግራፍ ብቻ መመልከት ዕጣ ፈንታችን ሲመስል ግን “ይደብራል”። የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር መሥራች የነበረች አገር (ለሦስት ዐሠርት ዐመታት ሙሉ) መሳተፍ እንኳን “እንዳማራት ሲቀር”፣ “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት” ያሰኛል። ግና፥ አዲሱ ትውልድ እንደ ብራ-ብራቅ ብጤ ድንገት በረቀ!
![]() |
ዋልያዎቹ |
እናም “ዋልያዎቹ” በማጣሪያው የነበረባቸውን ሰላማዊ ፍልሚያ በድል ተወጥተው ወደ ደቡብ አፍሪካ ዋንጫ የመግቢያ ትኬታቸውን ሊቈርጡ በቅተዋል። በተለይ ሱዳንን በመልሱ ጨዋታ 2-0 የረቱበት ዕለት የታየው ትንንቅ ለዚህ ትውልድ አይረሴ ነበር። ከዚያች ዕለት ጀምሮ፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሱ በመረጋገጡ መነጋገሪያ ርእስ ኾኖ ሰንብቷል። ተጫዋቾቹና የየዕለት እንቅስቃሴያቸው ሳይቀር በሀገር ውስጥም ኾነ በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን ሰፊ ሽፋን አግኝተው ቈይተዋል። (እዚህ ላይ፥ የአርሰናሉ አለቃ አርሰን ቬንገር በጋዜጣዊ መግለጫቸው የኢትዮጵያን ተሳትፎ አስመልክተው የሰጡትን አስተያየት ምን ያህል አጒነን ስናስጮኸው እንደከረምን ያስታውሷል።) አንዳንድ የኅትመት ሚዲያው አካላት መደበኛ ኅትመታቸውን ወደ ልዩ ዕትም ለውጠው ሰፊ ሽፋን ለመስጠት ሞክረዋል፤ መልካም ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች አዘጋጅቶ ካገኘው ገቢ (እንዳቅሙ) ጠቀም ያለ ስጦታ ለተጫዋቾቹና አሰልጣኞቻቸው ሸልሟል። መልካም ነውና ሊበረታታ ይገባዋል። ተጫዋቾቹ እዚህም፥ እዚያም እየተጋበዙ የተለያዩ በዓላትና ዝግጅቶች “ጌጥ” ኾነውም ነበር። በመጨረሻም፥ ቡድኑ በከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አደራና ማበረታቻ ተሰጥቶት በክብር ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሸኘ። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም “ነቅለው በመውጣት” ቡድኑን በድምቀት ሲቀበሉት ለተመለከተ፥ አካባቢው ጥምቀተ ባሕር እንጂ የጆሐንስበርግ አውሮፕላን ማረፊያ ነው ለማለት የሚያጠራጥር ነበር። ከዚህ በኋላ “ሜዳውም ፈረሱም ይኸው” ተብሎለት በፍልሚያው የሚያሳየው ውጤት ሲጠበቅ ነበር።
መድረስ አይቀርምና በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው ጥር 11 ደረሰ። 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫም በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት በይፋ ተከፈተ። ከመክፈቻው ዕለት በሣልስቱ ኢትዮጵያ በዕጣ በተደለደለችበት ቡድን-ሦስት ውስጥ የመጀመሪያውን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን ከአምናው ሻምፒዮን ቡድን ዛምቢያ ጋር ታደርጋለች። ዋልያ ከቺፖሎሎ ጋር የሚፋለምበት ግጥሚያ! ጥር 13 ቀን 2005 ዓ. ም ከምሽቱ 12፡00 ሠዓት ላይ!
እንግዲህ፥ ቀኑ ትናንትና መኾኑ ነው። ይህ ቀን፥ ማለትም ጥር 13፥ በታሪክ ከመዘገባቸው ጒዳዮች አንደኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቸኛ የዋንጫ ማንሣት ድሉን የቀመሰበት መኾኑ ነው። በቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመን ነው። የዛሬ 51 ዓመት በተመሳሳይ ቀን ጥር 13 ቀን፥ 1954 ዓ.ም.—ቦታ አዲስ አበባ ስታዲዮም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብጽ አቻውን በተጨማሪ ሠዓት 4 ለ 2 በኾነ ውጤት በመርታቱ፥ ኢትዮጵያ በዋንጫ ባለክብር ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ገባች። ይህም ለግማሽ ምእተ ዓመት ሳይለወጥ የቈየ ብቸኛ ታሪክ ኾኖ ቀረ። ኢትዮጵያ ከ3ኛው (1954) የአፍሪካ ዋንጫ በተጨማሪ 6ኛውን (1960) እና 10ኛውን (1968) የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ነበረች። በመጨረሻዎቹ ሁለቱ ጊዜያት ብሔራዊ ቡድኑ በዋንጫ ደጃፍ ላይ ተሳልሞ ቢያልፍም ሳይሳካለት ቀርቷል።
ከዚያ ውጭ የነበረው የመጨረሻ ተሳትፎው ሊቢያ ላይ በ1974 ዓ.ም ተዘጋጅቶ በነበረው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር። በዚያን ጊዜ፥ ቡድኑ ናይጄሪያ ዛምቢያና አልጀሪያ በሚገኙበት ምድብ ቤንጋዚ ከተማ ላይ ተደለደለ (ከአልጀሪያ በስተቀር [አሁን ቡርኪናፋሶ ደርሳናለች] ሁለቱ የዚያን ወቅት አሰናባቾቻችን ዘንድሮም አብረውን ተደልድለዋል)። ያኔ፥ ታዲያ ቡድናችን በምድብ ማጣሪያው ምንም ጐል ሳያስቈጥር፥ በመጀመሪያው ዙር በማለዳ ተሰናበተ። ይህ ከኾነበት ጊዜ ጀምሮ እንግዲህ መሬት ፀሐይን 31 ጊዜ ዞራታለች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቊጥርም በ 50 ሚሊዮን ጨምሯል፤ መንግሥታት ተፈራርቀዋል፤ ዓለማችንም ታላላቅ ለውጦች አስተናግዳለች፤ ቀዝቃዛቀው ጦርነት አብቅቶለታል፤ ሁለቱ ጀርመኖች ተዋሕደዋል፤ ናሚቢያ ነጻ ወጥታለች፤ አፓርታይድ ተወግዶ ደቡብ አፍሪካ የዓለምንም የአፍሪካንም ዋንጫ አዘጋጅታለች፤ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን የተባሉ ሁለት አገሮች ተፈጥረዋል፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ወደ አፍሪካ ኀብረት (AU) ተቀይሯል… ምን ያልኾነ አለ?
31 ዓመት ሙሉ ከተሳትፎ ርቆ መሰንበት ለመሥራች አገር አሳቃቂ ነበር። ለምሳሌ፥ የኔ ትውልድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ዐይቷት አያውቅም ነበር። ይህ ብቻም አይደለም። ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ግብ ካስቈጠረ 36 ዓመታት አልፈውበታል። ይህ ቡድን እኛ ስንወለድ ግብ ያስቈጠረ ቡድን ነው ማለት ነው። ለነገሩ፥ ሳይሳተፍ የት ሊያስቈጥር ይችላል? ዘንድሮ መጀመሪያ ላይ የምናየው ግብ እንግዲህ ከሦስት ደርዘን ዓመታት በኋላ በመቈጠሩ ሪከርድ የሚሰብር ነው። (ትናንት እንዳየነው፥ ይህን ታሪክ አዳነ ግርማ ወስዶታል።) እንግዲህ ይህን መሳይ ትልቅ ኀላፊነትን ተሸክሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዘው ቡድን በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ተኰትኲቶ ያደገ አልነበረም። አንድ አስረጅ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀስ፥ አባቶቻችን 20 ሚሊዮን ኾነው የሠሩት ስታዲዮም እኛ 80 ሚሊዮን ኾነን እየፈረሰ ባለበት ጊዜ የተነሣ በመኾኑ የቡድኑ ጥረት የሚደነቅ ነው። (በየክልሉ እየተሠሩ ያሉትን ስታዲዮሞች ዘንግቼ አይደለም፤ የእነርሱ ግንባታ ተስፋ ሰጪ ቢኾንም፥ ገና አገልግሎት እየሰጡ አይደለምና ነው።)
በአጠቃላይ ከላይ በዘረዘርናቸውና በሌሎችም ትብታቦች ተጠላልፎ የኖረው የሀገሬ ኳስ፥ ብሔራዊ ቡድናችን በድንገት ባሳየው መነቃቃትና ጥረት በአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በተቀረውም ዓለም ፊት “እኛም አለን” ሊል በቅቷል። ለዚህ ውጤት መገኘት የበኲላቸውን ጥረት ያደረጉት ተጫዋቾቻችንና አሠልጣኞቻቸው (የየክለብ አሠልጣኞቻቸውንም ላለመዘንጋት) ምስጋና ይገባቸዋል። ፌዴሬሽኑም ያቅሙን ያህል መንደፋደፉ አልቀረምና መበረታታት አለበት። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መነሣሣት “ሰለቸኝ” የማይለው ተመልካች መመስገን ይገባዋል፥ ይመስለኛል።
እንግዲህ እንደ ነፍሰ ጡር ቀን እየቈጠርን (ኢቴቪ ከዜና እወጃው ለጥቆ የሚያሳየውን አቈልቋይ-ቀን-ቈጠራ ያስታውሷል) ጥር 13ን ስንጠባበቅ እያለን ቀኑ ከተፍ አለ። ይህን ሳስብ፥ በተደጋጋሚ የሰማሁት አንድ ጨለምተኛ አባባል ከጆሮዬ እንደተደቀነ ከርሜ ነበር። ጨዋታውን ለማየት ስወጣም ይኸው “ነትራኪ” አባባል አልተለየኝም። “ለመሸነፍ እንዲህ መክለፍለፍ”። ይህን ሐሞት አፍሳሽ ብሒል በሌላ ለዘብተኛ ሐረግ ወደ ጐን ገፍቼ፥ ከቴሌቪዥኑ ገጸ ምስል (ስክሪን) ፊት ተሰየምሁ፦ “ለመሳተፍ፣ በጨዋነት መጣደፍ”።
የዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታ ግን አስደማሚ ኾኖ አረፈው። እኔም ዐይኔን ማመን አልቻልኩም ነበር። ወይስ “ለራስ ሲቆርሱ” ኾኖብኝ ስሜቴ እያጋነነብኝ ነው። ኧረ፥ አይመስለኝም! በዚያው የነበሩ የጨዋታው ተንታኞችን አለማመን አልችልማ! እነ ሰንዴ ኦሊሴይ ሰይቀሩ ቡድኑን ከባርሴሎና ክለብ አጨዋወት ጋር እስከማነጻጸር ርቀት ሄደው ነበር እኮ! በቃ፥ ኢትዮጵያውያኑ ኳስ መጫወት እንደሚችሉ ብቻ ሳይኾን፣ ጫናን ተቋቁመው ግብ በማስቈጠር ከባለፈው ዓመት ሻምፒዮን ጋር ነጥብ መጋራት በመቻላቸው መነጋገሪያ ኾነዋል። ብራቮ ዋልያዎች!!
ከዚህ በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቡድናቸውን ለማበረታታትና ድጋፍ ለመስጠት ትኬት ገዝተው፥ ረጅም መንገድ ተጒዘው፥ በልዩ ልዩ ሕብርና በሀገሪቱ ባንዲራ አሸብርቀው ከመገኘታቸውም በላይ ለቡድኑ የኋላ ደጀን ስለኾኑ እናመሰግናቸዋለን። በቀሪዎቹ ጨዋታዎችም ይህንኑ እንደሚደግሙት እንጠብ ቃለን።
ይህን ካልኩ በኋላ፥ ወደ አንዳንድ ትዝብታዊ ምልከታዬ ላዝግም። በትናንትናው ጨዋታ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መደሰቴን መደበቅ ባይቻለኝም፣ በአንዳንድ ጒዳዮች ማዘኔ ግን አልቀረም። ያዘንኩባቸው ነገሮች የተከሰቱበት ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ሕጋዊነትን፣ ሐቀኛነትን፣ ሰላምንና ወንድማማችነትን የሚያንኳስሱ ስለኾኑ ልንጸየፋቸው ይገባል ብዬ አምናለሁና የሚከተለውን እጫጭራለሁ። የተወሰኑትን ልጥቀስ መሰለኝ፡-
ይህን ካልኩ በኋላ፥ ወደ አንዳንድ ትዝብታዊ ምልከታዬ ላዝግም። በትናንትናው ጨዋታ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መደሰቴን መደበቅ ባይቻለኝም፣ በአንዳንድ ጒዳዮች ማዘኔ ግን አልቀረም። ያዘንኩባቸው ነገሮች የተከሰቱበት ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ሕጋዊነትን፣ ሐቀኛነትን፣ ሰላምንና ወንድማማችነትን የሚያንኳስሱ ስለኾኑ ልንጸየፋቸው ይገባል ብዬ አምናለሁና የሚከተለውን እጫጭራለሁ። የተወሰኑትን ልጥቀስ መሰለኝ፡-
የመጀመሪያው፥ አንድ ለናቱ የኾነውን ኢቴቪን ይመለከታል። እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ ነው። የትናንትናውን ጨዋታ የመጀመሪያ ግማሽ በዲ.ኤስ.ቲቪ ነበር ያየሁት። ይህ ያደረግሁት በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው በክፍያ ዋጋ መናር ምክንያት ኢቴቪ ጨዋታውን ላያስተላልፍ የመቻል አጋጣሚው ጠንከር ብሎ ስለታሰበኝ ነው (በርካታ የአፍሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የክፍያውን ከፍተኛነት አስመልክተው መቸገራቸውን መግለጻቸውን ከኢቴቪ አዳምጠናል)። ሌላው ደግሞ ከተሞክሮ የተማርኩት ነው። ይኸውም፣ የስፖንሰሮች ማስታወቂያ ለማሳየት ሲባል (የጨዋታ መጀመር እንኳ ሳያግደው) ቅጥ ባጣ መንገድ በማስታወቂያ ጋጋታ የሚያሰላቸንን ኢቴቪን ሽሽት ነው። አንዳንድ ጊዜማ ጨዋታውን የያዘውን የገጸ-ምስል (ስክሪኑን) ስፋት አሸማቅቆ በማጥበብ ጥግ ላይ ይሸነቅረውና ማስታወቂያውን ያስኮመኩመናል።
ብሸሸውም ግን አልቀረልኝም፤ ሳይመሽ ወደቤት ለመሄድ ፈልጌ ስለነበር ሁለተኛውን ግማሽ ጨዋታ በኢቴቪ ነበር ያየሁት። ግን አስደንጋጭ ነገር ለመስማትና ለማየት ተገድጃለሁ። ኢቴቪያችን ያለክፍያ ስርጭት ጠልፎ እያስተላለፈ መኾኑን የሚናገር ጽሑፍ በስክሪኑ ግርጌ መጥቶ ተደነቀረ። የጨዋታው ዘጋቢም (commentator) ሕጋዊ የኾነ ርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ሲያወሳ አደመጥሁ። እንዴት እንደ ደነገጥሁ አትጠይቁኝ። የቴሌሺዥን አገልግሎት ዓመታዊ ክፍያን አስመልክቶ ስለ ሕጋዊነት የሚለፍፈው ያገሬ ቴሌቪዢን ጣቢያ እንዲህ ዐይነት ተግባር በዘመናዊው ዓለም ዐይን ፊት ሲሠራ ሲታይ አለመሸማቀቅ እችል ነበር ወይ?
ሁለተኛው ምልከታዬ የሚያነጣጥረው በጨዋታው መኻል በደረሰ ጉዳትና እሱን ተከትሎ በተሰጡ አስተያየቶች ላይ ነው። በረኛችን ጀማል ጣሰው የመጨረሻ ሰው እንደመኾኑ የዛምቢያውን
አጥቂ ለማስቀረት የወሰነው ውሳኔ እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ያን ያህል እርግጫ በተጫዋቹ ብሽሽት ስር መሰንዘሩ አሳዛኝ ኾኖብኛል። ምን አደረገው?
ጀማል ራሱ ተጫዋች አይደለምን? ከኳስ ጋር በፍጥነት የመጣውን ተጫዋች በቀላል ግፊያ ብቻ ማቈም ይችልስ አልነበረም? የባሰው ደግሞ፥ ቀይ ካርድ ማየቱ የሚጠበቅ ብቻ ሳይኾን ትክክለኛ ርምጃ ኾኖ ሳለ፥ አንዳንድ ተመልካቾች ወዲያውኑ፥ አሠልጣኙ እና አንዳንድ የኤፍ. ኤም የኳስ ተንታኞች ደግሞ በማግስቱ፥ “በቢጫ ቢታለፍ ይበቃው ነበር” የሚል ማመቻመች ሲሰነዝሩ መስማቴ አሳዝኖኛል። ለዚያ ርግጫ ቀይ ካርድ ካልተሰጠ ገሶና ፋስ ይዞ እስኪገባ እንደመጠበቅ እቈጥረዋለሁ።
ኢትዮጵያዊ ብንኾንስ ኳስና መስመር የለቀቀ ጀብደኛነትን የመቀላቀልን ክፋት አለማውገዝ ይቻላል ወይ? ያ- ድርጊት የተፈጸመው በአዳነ፣ ወይም በሳልሀዲን ላይ ቢኾንስ ምን ይሰማን ነበር? ሊደረግብን የማንወደውን በሌሎች ላይ ማድረግ ዐመፃ አይደለምን? በቴሌቪዥን
መስኮት ጨዋታውን የሚያዩ ልጆቻችንስ በጒዳዩ ላይ የምንሰጠውን አስተያየት ሲሰሙ ምን ይማራሉ?
ሦስተኛው ትዝብቴ ጋሽ ሰውነት ላይ ይኾናል። ኢትዮጵያ በአዳነ ግርማ ግብ አቻ ከኾነች በኋላ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ተጫዋጮቹ ሠዓት የማባከን ሙከራዎች ሲያደረጉ ተመልክተናል (በግሌ ሠዓት ማባከን ሸር ይመስለኛል። ነገር ግን፥ ብዙውን ጊዜ፥ ማንኛውም ቡድን ውጤት ለማስጠበቅ ሠዓት ማባከንን እንደ አንድ ዘዴ ሲጠቀምበት ዐያለሁ። ስለዚህ፥ የእኛ ቡድን ላይ የተለየ ፍርድ ለመስጠት መቋመጤ አይደለም)። እኔን የገረመኝ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ለግብ ጠባቂው ዘርይሁን “የአልምጥልን” መመሪያ ሲያስተላልፉ፣ የካሜራ “ዐይን” እንደሚይዛቸው አለመገንዘባቸው ነው። በቀጥታ “ተኛና ሰንብት” ዐይነት ምልክት እያሳዩ ማመልከት ብቻ ሳይኾን፣ ዘርይሁን ከተነሣ በኋላ ተመልሶ ለጥ ሲል (ይመስለኛል) አውራጣታቸውን ቀስረው ማድነቃቸው አስገራሚ ኾኖብኛል። አዲስ አበባ ስታዲዮም ያሉ መስሏቸው ይሆን? እንደሚታወቀው፥ እኛ ሜዳ ላይ፥ እንኳን ያን መሠል ግላዊ ተግባር ይቅርና አንዳንዴ ጐል እንኳን በካሜራ ሳይያዝ ያመልጣል።
አራተኛውና የመጨረሻው ተመልካቹን (ደጋፊውን) ይመለከታል። በድጋፋች ላይ ነውጠኛነት ይታይበታል። እንደ ተከታተላችሁት፥ ዳኛው ቀይ ካርድ ለጀማል ካከናነቡት በኋላ፣ ተመልካቹ መስመር የለቀቀ ተቃውሞ አድርጓል። እንዲሁም ዛምቢያ አንድ ጐል ማግባቱን ተከትሎ ተጫዋቾቻቸው ደስታቸውን ሲገልጡ በነበረበት ወቅት (ምናልባት በኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ፊት ለፊት ሄደው ተተናኲሰው እንደኾን አላውቅም)፣ ደጋፊዎቻችን ቡቡዜላና የፕላስቲክ ጠርሙሶች ወደ ሜዳ እየወረወሩ ሲያብጡ መታየታቸው አሳፋሪ ነው። ብሔራዊ ፌዴሬሽናችን ሊያስቀጣ የሚችልም ድርጊት ነው። የስፖርቱ ዓለም የሚተዳደረው በጨዋታ ሕግና ደንብ ነው። በደልም ተፈጽሞ ሲገኝ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን ማሰማት፥ አቤቱታንም በሚመለከተው አካልና ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ መሠረት ማቅረብ እንጂ በጫካ ሕግ መነዳት ተገቢ አለመኾኑን የተገነዘብን አልመሰለኝም። እዚህ አለቅቅ ያለን አባዜ ተከትሎን በየሰዉ አገር መሄዱም አስገራሚ ኾኖብኛል። እዚያው በአካል ከተገኙት በተጨማሪ፥ በዙሪያዬ ኾነው በቴሌቪዥን መስኮት ጨዋታውን እየተመለከቱ ከነበሩት ደጋፊዎች መካከል ጥቂቶች፥ “በለው”፥ “ቀልጥመው” ሲሉ እሰማቸው ነበርና በኀዘን አስታውሳቸዋለሁ።
ይህን ሁሉ የምለው ሀገሬ አርበኛነት የሞላባት (Patriotic) መኾኗን ጠልቼው አይደለም። ችግር የለውም ትሁን። ነገር ግን፥ አርበኛነት በስሜት መንደድ ብቻ ነው እንዴ? ይህን የምለው ሀገራችን ስሜታዊነት ብቻ ሳይኾን ሕግና ሥርዓት የሰፈነባት መኾኗ ከመመሰጥ በላይ የግድ ስለሚያስፈልገን ነው። ሕግና ሥርዓትን ደግሞ በሁሉ ቦታ እየተለማመድን ተንከባክበን የምናጠናክረው እሴት ነው። ይህን የምጽፈው ልጄ የምትኖርበት ዓለም የጡጫና የርግጫ ድባብ እንደ መርግ የተጫነው እንዳይኾን ለመከላለል በነገር ሁሉ የድርሻዬን ለመወጣት እንድችል ልጄን የማስተማር ኀላፊነት ስላለብኝ ነው። የዜግነት መብቴ እንዲከበር መጮኽ የምችለው፥ ሕግን የማክበርና የማስከበር ዜግነታዊ ግዴታዬን የተወጣሁ እንደኾነ ነው።
ሕግን ለማክበር ደግሞ በፖሊስ ጣቢያ ፊት ማለፍ የለብንም። የሕግ ልዕልናና ክቡርነት የሚታሰበን የደንብ ልብሱ ተጐናጽፎ የቈመ ሰውዬ፥ ወይም የታጠቀ ጸጥታ አስከባሪ ስናይ ብቻ ሊኾን አይገባውም። ይህ ሀገር የሚተዳደረው በሕግ የበላይነት (by the Law of the Land) ስለኾነ ነው እንጂ። የትራፊክ ደንቦችን የምናከብረው የትራፊክ ፖሊሱን በመንገድ ዳር መገኘት ዐይተንና አጠያይቀን ከኾነ በጣም አሳዛኝ ግብዞች ነን። ሕግን ተደብቀንም ቢኾን ማክበር ይኖርብናል። ሰው አየኝ አላየኝ ብለን ሳይኾን፣ ሕግ ስለኾነ ብቻ መከበር ይኖርበታል። ያን ጊዜ ለሕግ ልዕልና መጐልበት የድርሻችንን እንደተወጣን ይቈጠራል።
ሕግን ለማክበር ደግሞ በፖሊስ ጣቢያ ፊት ማለፍ የለብንም። የሕግ ልዕልናና ክቡርነት የሚታሰበን የደንብ ልብሱ ተጐናጽፎ የቈመ ሰውዬ፥ ወይም የታጠቀ ጸጥታ አስከባሪ ስናይ ብቻ ሊኾን አይገባውም። ይህ ሀገር የሚተዳደረው በሕግ የበላይነት (by the Law of the Land) ስለኾነ ነው እንጂ። የትራፊክ ደንቦችን የምናከብረው የትራፊክ ፖሊሱን በመንገድ ዳር መገኘት ዐይተንና አጠያይቀን ከኾነ በጣም አሳዛኝ ግብዞች ነን። ሕግን ተደብቀንም ቢኾን ማክበር ይኖርብናል። ሰው አየኝ አላየኝ ብለን ሳይኾን፣ ሕግ ስለኾነ ብቻ መከበር ይኖርበታል። ያን ጊዜ ለሕግ ልዕልና መጐልበት የድርሻችንን እንደተወጣን ይቈጠራል።
እግር ኳስ ስሜትን የሚገዛ ጨዋታ ነው። እውነት ነው። ግን ያ ስሜት ብቻውን እንዳሻው የሚነዳን ፍጡራን አይደለንም። በጨዋታው እየተዝናናን ሳለን፥ ለስሜት ብቻ ሳይኾን ለእውነትም ስፍራ ይኑረን። በልጆቻችን ፊት ሚዛን የሳተ አስተያየት እየሰጠን የምንመለከተው ጨዋታ የልጆቻችንን ባሕርይ እንዴት እንደሚቀርጽ ማስተዋል ብልኅነት ነው። ሌላው ቊም ነገር ኳስ መጫወት ዓላማው ወዳጅነትን፥ ሰላምን፥ የጋራ ትብብርንና ዘላቂ ወዳጅነትን ለማበረታት እንጂ ጠላት ለማደራጀትና ባላንጣን ለማዋረድ ተደርጐ መታሰብ የለበትም። ብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹም ኾኑ ክፍላተ ዓለማዊ ኮንፌዴሬሽኖቹ የተቋቋሙት ለነዚሁ ሠናይ ዓላማዎች ነው። Fair Play የተሰኘውን መልካም ዕሴት እናበረታታ!
መልካም ውጤት ለዋልያዎቹ!
ሻሎም!
It is a very good observation and reflection! I like your way of writing and creativity. Your writing is artistic.
ReplyDeleteyour admirer from Malawi